• 1. አል-ረሕማን፤

  • 2. ቁርኣንን አስተማረ፡፡

  • 3. ሰውን ፈጠረ፡፡

  • 4. መናገርን አስተማረው፡፡

  • 5. ፀሐይና ጨረቃ በተወሰነ ልክ (ይኼዳሉ)፡፡

  • 6. ሐረግና ዛፍም (ለእርሱ) ይሰግዳሉ፡፡

  • 7. ሰማይንም አጓናት፡፡ ትክክለኛነትንም ደነገገ፡፡

  • 8. በሚዛን (ስትመዝኑ) እንዳትበድሉ፡፡

  • 9. መመዘንንም በትክክል መዝኑ፡፡ ተመዛኙንም አታጉድሉ፡፡

  • 10. ምድርንም ለፍጡሩ አደላደላት፡፡

  • 11. በውስጧ እሸት ባለ ሺፋኖች የኾኑ ዘንባባዎችም ያሉባት ስትኾን፡፡

  • 12. የገለባ ባለቤት የኾነ ቅንጣትም፡፡ ባለ መልካም መዐዛ ቅጠሎችም (ያሉባት ስትኾን)፡፡

  • 13. (ሰዎችና ጋኔኖች ሆይ!) ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 14. ሰውን እንደ ሸክላ ከሚቅጨለጨል ደረቅ ጭቃ ፈጠረው፡፡

  • 15. ጃንንም ከእሳት ከኾነ ነበልባል ፈጠረው፡፡

  • 16. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 17. የሁለቱ ምሥራቆች ጌታ፤ የሁለቱ ምዕራቦችም ጌታ ነው፡፡

  • 18. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 19. ሁለቱን ባሕሮች የሚገናኙ ሲኾኑ ለቀቃቸው፡፡

  • 20. (እንዳይዋሐዱ) በመካከላቸው ጋራጅ አልለ፡፡ (አንዱ ባንዱ ላይ) ወሰን አያልፉም፡፡

  • 21. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታሰተባብላላችሁ?›

  • 22. ሉልና መርጃን ከሁለቱ ይወጣል፡፡

  • 23. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 24. እንደ ጋራዎች ኾነው በባሕር ውስጥ የተሠሩት ተንሻለዮቹም (ታንኳዎች) የእርሱ ናቸው፡፡

  • 25. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 26. በእርሷ (በምድር) ላይ ያለው ሁሉ ጠፊ ነው፡፡

  • 27. የልቅናና የልግሥና ባለቤት የኾነው የጌታህ ፊትም ይቀራል፡፡ (አይጠፋም)፡፡

  • 28. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 29. በሰማያትና በምድር ውስጥ ያሉት ሁሉ ይለምኑታል፡፡ በየቀኑ ሁሉ እርሱ በሥራ ላይ ነው፡፡

  • 30. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታሰተባብላላችሁ?›

  • 31. እናንተ ሁለት ከባዶች (ሰዎችና ጋኔኖች) ሆይ! ለእናንተ (መቆጣጠር) በእርግጥ እናስባለን፡፡

  • 32. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 33. የጋኔንና የሰው ጭፍሮች ሆይ! ከሰማያትና ከምድር ቀበሌዎች መውጣትን ብትችሉ ውጡ፡፡ በስልጣን እንጅ አትወጡም፡፡ (ግን ስልጣን የላችሁም)

  • 34. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 35. በሁለታችሁም ላይ ከእሳት ነበልባል፣ ጭስም ይላክባችኋል፡፡ (ሁለታችሁም) አትርረዱምም፡፡

  • 36. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 37. ሰማይም በተሰነጠቀችና እንደ ጽጌረዳ፣ እንደታረበ ቆዳ በኾነች ጊዜ፤ (ጭንቁን ምን አበረታው)፡፡

  • 38. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 39. በዚያም ቀን ሰውም ጃንም ከኃጢኣቱ ገና አይጠየቅም፡፡

  • 40. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 41. ከሓዲዎች በምልክታቸው ይታወቃሉ፡፡ አናቶቻቸውንና ጫማዎቻቸውንም ይያዛሉ፡፡

  • 42. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ፡፡

  • 43. ይህቺ ያቺ አመጸኞች በእርሷ ያስተባብሉባት የነበረችው ገሀነም ናት (ይባላሉ)፡፡

  • 44. በእርሷና በጣም ሞቃት በኾነ ፍል ውሃ መካከል ይመላለሳሉ፡፡

  • 45. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 46. በጌታውም ፊት መቆምን ለፈራ ሰው ሁለት ገነቶች አልሉት፡፡

  • 47. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 48. የቀንዘሎች ባለ ቤቶች የኾኑ (ገነቶች አልሉት)፡፡

  • 49. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 50. በሁለቱ ውስጥ የሚፈስሱ ሁለት ምንጮች አልሉ፡፡

  • 51. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 52. በሁለቱ ውስጥ ከፍራፍሬዎች ሁሉ ሁለት ዓይነቶች (እርጥብና ደረቅ) አልሉ፡፡

  • 53. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 54. የውስጥ ጉስጉሳቸው ከወፍራም ሐር በኾኑ ምንጣፎች ላይ የተመቻቹ ሲኾኑ (ይንፈላሰሳሉ)፡፡ የሁለቱም ገነቶች ፍሬ (ለለቃሚ) ቅርብ ነው፡፡

  • 55. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 56. በውስጣቸው ከበፊታቸው (ከባሎቻቸው በፊት) ሰውም ጃንም ያልገሰሳቸው ዓይኖቻቸውን (በባሎቻቸው ላይ) አሳጣሪዎች (ሴቶች) አልሉ፡፡

  • 57. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 58. ልክ ያቁትና መርጃን ይመስላሉ፡፡

  • 59. ከጌታችሁም ጸጋዎቸ በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 60. የበጎ ሥራ ዋጋ በጎ እንጅ ሌላ ነውን?

  • 61. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 62. ከሁለቱ ገነቶችም ሌላ ሁለት ገነቶች አልሉ፡፡

  • 63. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?›

  • 64. ከልምላሜያቸው የተነሳ ወደ ጥቁረት ያዘነበሉ ናቸው፡፡

  • 65. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 66. በውስጣቸው ሁለት የሚንፏፉ ምንጮች አልሉ፡፡

  • 67. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 68. በውስጣቸው ፍራፍሬ፣ ዘምባባም፣ ሩማንም አልለ፡፡

  • 69. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 70. በውስጣቸው ጠባየ መልካሞች መልክ ውቦች (ሴቶች) አልሉ፡፡

  • 71. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 72. በድንኳኖች ውስጥ የተጨጎሉ የዓይኖቻቸው ጥቁረትና ንጣት ደማቅ የኾኑ ናቸው፡፡

  • 73. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 74. ከነርሱ በፊት ሰውም ጃንም አልገሰሳቸውም፡፡

  • 75. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባበላላችሁ?

  • 76. በሚያረገርጉ አረንጓዴ ምንጣፎችና በሚያማምሩ ስጋጃዎች ላይ የተደላደሉ ሲኾኑ (ይቀመጣሉ)፡፡

  • 77. ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?

  • 78. የግርማና የመክበር ባለቤት የኾነው ጌታህ ስም ተባረከ፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo