• 1. ያ ንግሥና በእጁ የኾነው አምላክ ችሮታው በዛ፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

  • 2. ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፡፡ እርሱም አሸናፊው መሓሪው ነው፡፡

  • 3. ያ ሰባትን ሰማያት የተነባበሩ ኾነው የፈጠረ ነው፡፡ በአልረሕማን አፈጣጠር ውስጥ ምንም መዛነፍን አታይም፡፡ ዓይንህንም መልስ፡፡ «ከስንጥቆች አንዳችን ታያለህን?»

  • 4. ከዚያም ብዙ ጊዜ ዓይንህን መላልስ፡፡ ዓይንህ ተዋርዶ እርሱም የደከመ ኾኖ ወዳንተ ይመለሳል፡፡

  • 5. ቅርቢቱን ሰማይም በእርግጥ በመብራቶች (በከዋክብት) አጌጥናት፡፡ ለሰይጣናትም መቀጥቀጫዎች አደረግናት፡፡ ለእነርሱም (ለሰይጣኖች) የእሳትን ቅጣት አዘጋጀን፡፡

  • 6. ለእነዚያም በጌታቸው ለካዱት የገሀነም ቅጣት አልላቸው፡፡ መመለሻይቱም ከፋች!

  • 7. በውስጧ በተጣሉ ጊዜ፤ እርሷ የምትፈላ ስትኾን ለእርሷ (እንደ አህያ) ማናፋትን ይሰማሉ፡፡

  • 8. ከቁጭትዋ የተነሳ ልትቆራረጥ ትቀርባለች፡፡ በውስጧ ጭፍሮች በተጣሉ ቁጥር ዘበኞችዋ «አስፈራሪ (ነቢይ) አልመጣችሁምን?» በማለት ይጠይቋቸዋል፡፡

  • 9. «አይደለም በእርግጥ አስፈራሪ መጥቶናል፡፡ አስተባበልንም፡፡ አላህም ምንንም አላወረደ እናንተ (አውርዷል ስትሉ) በትልቅ ስህተት ውስጥ እንጅ አይደላችሁም አልን» ይላሉ፡፡

  • 10. «የምንሰማ ወይም የምናስብ በነበርንም ኖሮ በነዳጅ እሳት ጓዶች ውስጥ ባልኾን ነበር» ይላሉ፡፡

  • 11. በኀጢኣታቸውም ያምናሉ ለእሳት ጓዶችም (ከእዝነት) መራቅ ተገባቸው፡፡

  • 12. እነዚያ ጌታቸውን በሩቁ የሚፈሩ ለእነርሱ ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አልላቸው፡፡

  • 13. (ሰዎች ሆይ!) ቃላችሁንም መስጥሩ፡፡ ወይም በእርሱ ጩሁ፡፡ እርሱ በልቦች ውስጥ ያለን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡

  • 14. የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀት ረቂቁ፣ ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን?

  • 15. እርሱ ያ ምድርን ለእናንተ የተገራች ያደረገላችሁ ነው፡፡ በጋራዎችዋና በመንገዶችዋም ኺዱ፡፡፡ ከሲሳዩም ብሉ፡፡ (ኋላ) መመለሻውም ወደእርሱ ብቻ ነው፡፡

  • 16. በሰማይ ውስጥ ያለን (ሰራዊት) በእናንተ ምድርን ቢደረባባችሁ ወዲያውም እርሷ የምታረገርግ ብትኾን ትተማመናላችሁን? (አትፈሩምን?)

  • 17. ወይም በሰማይ ውስጥ ያለን በእናንተ ላይ ጠጠርን ያዘለች ነፋስን ቢልክባችሁ ትተማመናላችሁን? (አትፈሩምን?) ማስጠንቀቄም እንዴት እንደኾነ ወደፊት ታውቃላችሁ፡፡

  • 18. እነዚያም ከእነርሱ በፊት የነበሩት በእርግጥ አስተባበሉ፡፡ ጥላቻዬም እንዴት ነበር!

  • 19. ወደ አእዋፍ ከበላያቸው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ተንሳፋፊዎች የሚሰበሰቡም ሲኾኑ አላዩምን? ከአልረሕማን በቀር (ባየር ላይ) የሚይዛቸው የለም፡፡ እርሱ በነገሩ ሁሉ ተመልካች ነው፡፡

  • 20. በእውነቱ ያ እርሱ ከአልረሕማን ሌላ የሚረዳችሁ ለእናንተ የኾነ ሰራዊት ማነው? ከሓዲዎች በመታለል ውስጥ እንጅ በሌላ ላይ አይደሉም፡፡

  • 21. ወይም ሲሳዩን ቢይዝባችሁ ያ ሲሳይን የሚሰጣችሁ ማነው? በእውነቱ እነርሱ በሞገድና በመደንበር ውስጥ ችክ አሉ፡፡

  • 22. በፊቱ ላይ ተደፍቶ የሚኼድ ሰው ይበልጥ የቀና ነውን? ወይስ በቀጥተኛ መንገድ ላይ ተስተካክሎ የሚኼድ?

  • 23. «እርሱ ያ የፈጠራችሁ ለእናንተም መስሚያና ማያዎችን፣ ልቦችንም ያደረገላችሁ ነው፡፡ ጥቂትንም አታመስግኑም» በላቸው፡፡

  • 24. «እርሱ ያ በምድር ላይ የበተናቸሁ ነው፡፡ ወደእርሱም ትሰበሰባላችሁ» በላቸው፡፡

  • 25. «እውነተኞችም እንደኾናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡

  • 26. «ዕውቀቱ አላህ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም» በላቸው፡፡

  • 27. (ቅጣቱን) ቅርብ ኾኖ ባዩትም ጊዜ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ፊቶች ይክከፋሉ፡፡ «ይህ ያ በእርሱ ትከራከሩበት የነበራችሁት ነው» ይባላሉም፡፡

  • 28. «አያችሁን? አላህ ቢገድለኝ ከእኔ ጋር ያሉትንም (እንደዚሁ) ወይም (በማቆየት) ቢያዝንልን ከሓዲዎችን ከአሳማሚ ቅጣት የሚያድን ማን ነው?» በላቸው፡፡

  • 29. «እርሱ (እመኑበት የምላችሁ) አልረሕማን ነው፡፡ (እኛ) በእርሱ አመንን፡፡ በርሱም ላይ ተጠጋን፡፡ ወደ ፊትም በግልጽ መሳሳት ውስጥ የኾነው እርሱ ማን አንደ ኾነ በእርግጥ ታውቃላችሁ» በላቸው፡፡

  • 30. «አያችሁን? ውሃችሁ ሠራጊ ቢኾን ፈሳሺን ውሃ የሚያመጣላቸሁ ማን ነው?» በላቸው፡፡ (አላህ የዓለማት ጌታ ያመጣዋል)፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo