• 1. እኛ ኑሕን «ሕዝቦችህን አሳማሚ ቅጣት ሳይመጣባቸው በፊት አስጠንቅቅ በማለት ወደ ሕዝቦቹ ላክነው፡፡»

  • 2. (እርሱም) አለ «ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ለእናንተ ገላጭ የኾንኩ አስጠንቃቂ ነኝ፡፡

  • 3. «አላህን ተገዙት፣ ፍሩትም፣ ታዘዙኝም በማለት፤ (አስጠንቃቂ ነኝ)፡፡

  • 4. «ለእናንተ ከኀጢኣቶቻችሁ ይምራልና፡፡ ወደተወሰነው ጊዜም ያቆያችኋል፡፡ የአላህ (የወሰነው) ጊዜ በመጣ ወቅት አይቆይም፡፡ የምታውቁት ብትኾኑ ኖሮ (በታዘዛችሁ ነበር)፡፡»

  • 5. (ስለ ተቃወሙትም) «አለ ጌታዬ ሆይ! እኔ ሌሊትም ቀንም ሕዝቦቼን ጠራሁ፡፡

  • 6. «ጥሪየም መሸሽን እንጅ ሌላ አልጨመረላቸውም፡፡

  • 7. «እኔም ለእነርሱ ትምር ዘንድ (ወደ እምነት) በጠራኋቸው ቁጥር ጣቶቻቸውን በጆሮዎቻቸው ውስጥ አደረጉ፡፡ ልብሶቻቸውንም ተከናነቡ፡፡ (በመጥፎ ሥራቸው ላይ) ዘወተሩም፡፡ (ያለ ልክ) መኩራትንም ኮሩ፡፡

  • 8. «ከዚያም እኔ በጩኸት ጠራኋቸው፡፡

  • 9. «ከዚያም እኔ ለእነርሱ ገለጽኩ፡፡ ለእነርሱም መመስጠርን መሰጠርኩ

  • 10. «አልኳቸውም፡- ጌታችሁን ምሕረትን ለምኑት፡፡ እርሱ በጣም መሐሪ ነውና፡፡

  • 11. «በእናንተ ላይ ዝናምን ተከታታይ አድርጎ ይልካል፡፡

  • 12. «በገንዘቦችና በልጆችም ይለግሰላችኋል፡፡ ለእናንተም አትክልቶችን ያደርግላችኋል፡፡ ለእናንተም ወንዞችን ያደርግላችኋል፡፡»

  • 13. ለአላህ ልቅናን የማትሹት ለእናንተ ምን አላችሁ?

  • 14. በልዩ ልዩ ኹኔታዎች በእርግጥ የፈጠራችሁ ሲኾን፡፡

  • 15. አላህ ሰባትን ሰማያት አንዱ ካንዱ በላይ ሲኾን እንዴት እንደፈጠረ አታዩምን?

  • 16. በውስጣቸውም ጨረቃን አብሪ አደረገ፡፡ ፀሐይንም ብርሃን አደረገ፡፡

  • 17. አላህም ከምድር ማብቀልን አበቀላችሁ፡፡

  • 18. ከዚያም በውስጧ ይመልሳችኋል፡፡ ማውጣትንም ያወጣችኋል፡፡

  • 19. አላህም ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ አደረጋት፡፡

  • 20. ከእርሷ ሰፋፊዎችን መንገዶች ትገቡ ዘንድ፡፡

  • 21. ኑሕ አለ፡- «ጌታዬ ሆይ! እነሱ አምመጹብኝ፡፡ ገንዘቡና ልጁም ከጥፋት በስተቀር ያልጨመረለትን ሰው ተከተሉ፡፡

  • 22. «ታላቅንም ተንኮል የመከሩትን ሰዎች» (ተከተሉ)፡፡

  • 23. አሉም «አምላኮቻችሁን አትተዉ፡፡ ወድንም፣ ሱዋዕንም፣ የጉሥንም፣ የዑቅንም ነስርንም አትተው፡፡

  • 24. «በእርግጥም ብዙዎችን አሳሳቱ፡፡ ከሓዲዎችንም ጥመትን እንጅ ሌላን አትጨምርላቸው» (አለ)፡፡

  • 25. በኀጢኣቶቻቸው ምክንያት ተሰጠሙ፡፡ እሳትንም እንዲገቡ ተደረጉ፡፡ ለእነርሱም ከአላህ ሌላ የኾኑ ረዳቶችን አላገኙም፡፡

  • 26. ኑሕም አለ «ጌታዬ ሆይ! ከከሓዲዎቹ በምድር ላይ አንድንም አትተው፡፡

  • 27. «አንተ ብትተዋቸው ባሮችህን ያሳስታሉና፡፡ ኀጢኣተኛ ከሓዲንም እንጅ ሌላን አይወልዱም፡፡

  • 28. «ጌታዬ ሆይ! ለእኔም ለወላጆቼም ምእመን ኾኖ በቤቴ ለገባም ሰው ሁሉ ለምእመናንና ለምእምናትም ምሕረት አድርግ፡፡ ከሓዲዎችንም ከጥፋት በቀር አትጨምርላቸው፤» (አለ)፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo