• 1. ለሰላቢዎች ወዮላቸው፡፡

  • 2. ለእነዚያ ከሰዎች ባስሰፈሩ ጊዜ የሚያስሞሉ፡፡

  • 3. ለእነርሱም (ለሰዎቹ) በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ የሚያጎድሉ (ለኾኑት)፡፡

  • 4. እነዚያ እነርሱ ተቀስቃሾች መኾናቸውን አያውቁምን?

  • 5. በታላቁ ቀን፡፡

  • 6. ሰዎች ሁሉ ለዓለማት ጌታ (ፍርድ)፤ በሚቆሙበት ቀን (ተቀስቃሾች መኾናቸውን)፡፡

  • 7. በእውነት የከሓዲዎቹ (የሰላቢዎቹ) መጽሐፍ በእርግጥ በሲጂን ውስጥ ነው፡፡

  • 8. ሲጂንም ምን እንደ ኾነ ምን አሳወቀህ?

  • 9. የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡

  • 10. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡

  • 11. ለእነዚያ በፍርዱ ቀን ለሚያስተባብሉት፡፡

  • 12. በእርሱም ወሰን አላፊ ኀጢአተኛ ሁሉ እንጅ ሌላ አያስተባብልም፡፡

  • 13. አንቀጾቻችን በእርሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናቸው» ይላል፡፡

  • 14. ይከልከል፤ ይልቁንም በልቦቻቸው ላይ ይሠሩት የነበሩት (ኀጢአት) ደገደገባቸው፡፡

  • 15. ይከልከሉ፤ እነርሱ በዚያ ቀን ከጌታቸው (ማየት) ተጋራጆች ናቸው፡፡

  • 16. ከዚያም እነርሱ በእርግጥ ገሀነምን ገቢዎች ናቸው፡፡

  • 17. ከዚያም «ይህ ያ በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁት ነው» ይባላሉ፡፡

  • 18. በእውነቱ የእውነተኞቹ ምእምናን መጽሐፍ በዒሊዮን ውስጥ ነው፡፡

  • 19. ዒሊዮንም ምን እንደ ኾነ ምን አሳወቀህ?

  • 20. የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡

  • 21. ባለሟልዎቹ ይጣዱታል፡፡

  • 22. እውነተኞቹ ምእምናን በእርግጥ በድሎት (ገነት) ውስጥ ናቸው፡፡

  • 23. በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ኾነው ይመለከታሉ፡፡

  • 24. በፊቶቻቸው ላይ የድሎትን ውበት ታውቃለህ፡፡

  • 25. ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጠጣሉ፡፡

  • 26. ማተሚያው ምስክ ከኾነ፤ በዚህም ተሽቀዳዳሚዎች ይሽቀዳደሙ፡፡

  • 27. መበረዣውም ከተስኒም ነው፡፡

  • 28. ባለሟሎቹ ከእርሷ የሚጠጡላት ምንጭ ናት፡፡

  • 29. እነዚያ ያምመጹት በእነዚያ ባመኑት በእርግጥ ይስቁ ነበሩ፡፡

  • 30. በእነርሱም ላይ ባለፉ ጊዜ ይጠቃቀሱ ነበር፡፡

  • 31. ወደ ቤተሰቦቻቸውም በተመለሱ ጊዜ (በመሳለቃቸው) ተደሳቾች ኾነው ይመለሱ ነበር፡፡

  • 32. ባዩዋቸውም ጊዜ «እነዚህ በእርግጥ ተሳሳቾች ናቸው» ይሉ ነበር፡፡

  • 33. በነርሱ ላይ ተጠባባቂዎች ተደርገው ያልተላኩ ሲኾኑ፡፡

  • 34. ዛሬ (በትንሣኤ ቀን) እነዚያ ያመኑት በከሓዲዎቹ ይስቃሉ፡፡

  • 35. በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ኾነው የሚመለከቱ ሲኾኑ (ይስቃሉ)፡፡

  • 36. ከሓዲዎች ይሠሩት የነበሩትን (ዋጋ) ተመነዱን? (ይላሉ)፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo