• 1. በሰው ላይ የሚታወስ ነገር ሳይኾን ከዘመናት የተወሰነ ጊዜ በእርግጥ አልፎበታል፡፡

  • 2. እኛ ሰውን (በሕግ ግዳጅ) የምንሞከረው ስንኾን ቅልቅሎች ከኾኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነው፡፡ ሰሚ ተመልካችም አደረግነው፡፡

  • 3. እኛ ወይ አመስጋኝ ወይም ከሓዲ ሲኾን መንገዱን መራነው፤ (ገለጽንለት)፡፡

  • 4. እኛ ለከሓዲዎች ሰንሰሎቶችንና እንዛዝላዎችን፣ እሳትንም አዘጋጅተናል፡፡

  • 5. በጎ አድራጊዎች መበረዣዋ ካፉር ከኾነች ጠጅ ይጠጣሉ፡፡

  • 6. ከእርሷ የአላህ ባሮች የሚጠጡላት (ወደፈለጉበት) ማንቧቧትን የሚያንቧቧት ከኾነች ምንጭ (ይጠጣሉ)፡፡

  • 7. (ዛሬ) በስለታቸው ይሞላሉ፡፡ መከራው ተሰራጪ የኾነንም ቀን ይፈራሉ፡፡

  • 8. ምግብንም ከመውደዳቸው ጋር ለድኻ፣ ለየቲምም፣ ለምርኮኛም ለእስረኛም ያበላሉ፡፡

  • 9. «የምናበላችሁ ለአላህ ውዴታ ብቻ ነው፡፡ ከእናንተ ዋጋንም ማመስገንንም አንፈልግም፡፡

  • 10. «እኛ (ፊትን) የሚያጨፈግግን ብርቱ ቀን ከጌታችን እንፈራለንና፤» (ይላሉ)፡፡

  • 11. አላህም የዚያን ቀን ክፋት ጠበቃቸው፡፡ (ፊታቸው) ማማርንና መደሰትንም ገጠማቸው፡፡

  • 12. በመታገሣቸውም ገነትንና የሐር ልብስን መነዳቸው፡፡

  • 13. በውስጧ በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች በውስጧ ፀሐይንም ጨረቃንም የማያዩ ሲኾኑ፡፡

  • 14. ዛፎችዋም በእነርሱ ላይ የቀረበች፣ ፍሬዎችዋም (ለለቃሚዎች) መግገራትን የተገራች ስትኾን (ገነትን መነዳቸው)፡፡

  • 15. በእነርሱም ላይ ከብር በኾኑ ዕቃዎች (ሰሐኖች) የብርጭቆዎች በኾኑ ኩባያዎችም ይዝዞርባቸዋል፡፡

  • 16. መለካትን የለኳቸው በኾኑ የብር ብርጭቆዎች (ይዝዞርባቸዋል)፡፡

  • 17. በእርሷም መበረዣዋ ዘንጀቢል የኾነችን ጠጅ ይጠጣሉ፡፡

  • 18. በውስጧ ያለችውን ሰልሰቢል ተብላ የምትጠራውን ምንጭ፡፡

  • 19. በእነርሱም ላይ (ባሉበት ኹነታ) የሚዘወትሩ ወጣት ልጆች ይዘዋወራሉ፡፡ ባየሃቸው ጊዜ የተበተነ ሉል ናቸው ብለህ ታስባቸዋለህ፡፡

  • 20. እዚያም በተመለከትክ ጊዜ ጸጋንና ታላቅ ንግሥናን ታያለህ፡፡

  • 21. አረንጓዴዎች የኾኑ የቀጭን ሐር ልብሶችና ወፍራም ሐርም በላያቸው ላይ አልለ፡፡ ከብር የኾኑ አንባሮችንም ይሸለማሉ፡፡ ጌታቸውም አጥሪ የኾነን መጠጥ ያጠጣቸዋል፡፡

  • 22. «ይህ በእርግጥ ለእናንተ ዋጋ ኾነ፡፡ ሥራችሁም ምስጉን ኾነ፤» (ይባላሉ)፡፡

  • 23. እኛ ቁርኣንን ባንተ ላይ ማውረድን እኛው አወረድነው፡፡

  • 24. ለጌታህ ፍርድም ታገሥ፡፡ ከእነርሱም ኀጢአተኛን ወይም ከሓዲን አትታዘዝ፡፡

  • 25. የጌታህንም ስም በጧትና ከቀትር በላይ አውሳ፡፡

  • 26. ከሌሊቱም ለእርሱ ስገድ፡፡ በረዢም ሌሊትም አወድሰው፡፡

  • 27. እነዚያ ፈጣኒቱን ዓለም ይወዳሉ፡፡ ከባድን ቀንም በስተፊታቸው ኾኖ ይተዋሉ፡፡

  • 28. እኛ ፈጠርናቸው፡፡ መለያልያቸውንም አጠነከርን፡፡ በሻንም ጊዜ መሰሎቻቸውን መለወጥን እንለውጣለን፡፡

  • 29. ይህቺ መገሠጫ ናት፡፡ የሻም ሰው ወደ ጌታው መንገድን ይይዛል፡፡

  • 30. አላህም ካልሻ በስተቀር አትሹም፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡

  • 31. የሚሻውን ሰው በእዝነቱ ውስጥ ያገባዋል፡፡ በዳዮቹንም (ዝቶባቸዋል)፡፡ ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣትን አዘጋጅቶላቸዋል፡፡

ሼር ያድርጉ
logo
logo
logo
logo