72. سورة الجن - ቁርዓን
- 1. (ሙሐመድ ሆይ!) በል «እነሆ ከጂን የኾኑ ጭፈሮች (ቁርኣንን) አዳመጡ፡፡‹እኛ አስደናቂ የኾነን ቁርኣን ሰማንም› አሉ ማለት ወደእኔ ተወረደ፡፡
- 2. ‹ወደ ቀጥታ መንገድ የሚመራን (ቁርአን ሰማን)፡፡ በእርሱም አመንን፡፡ በጌታችንም አንድንም አናጋራም፡፡›
- 3. ‹እነሆም የጌታችን ክብር ላቀ፡፡ ሚስትንም ልጅንም አልያዘም፡፡›
- 4. ‹እነሆም ቂላችን በአላህ ላይ ወሰን ያለፈን (ውሸት) ይናገር ነበር፡፡›
- 5. ‹እኛም ሰዎችና ጋኔኖች በአላህ ላይ ውሸትን (ቃል) አይናገሩም ማለትን ጠረጠርን፡፡›
- 6. ‹እነሆም ከሰዎች የኾኑ ወንዶች በጋኔን ወንዶች ይጠበቁ ነበሩ፡፡ ኩራትንም ጨመሩዋቸው፡፡›
- 7. ‹እነርሱም አላህ አንድንም አይቀሰቅስም ማለትን እንደጠረጠራችሁ ጠረጠሩ፡፡›
- 8. ‹እኛም ሰማይን (ለመድረስ) ፈለግን፡፡ ብርቱ ጠባቂዎችንና ችቦዎችንም ተሞልታ አገኘናት፡፡
- 9. ‹እኛም ከእርሷ (ወሬን) ለማደመጥ በመቀመጫዎች እንቀመጥ ነበርን፡፡ አሁን ግን የሚያዳምጥ ሰው ለእርሱ ተጠባባቂ ችቦን ያገኛል፡፡
- 10. ‹እኛም በምድር ውስጥ ባልሉ ሰዎች ክፉ ተሽቷል? ወይስ በእነርሱ ጌታቸው ደግን ነገር ሽቷል? ማለትን አናውቅም፡፡
- 11. ‹እኛም ከእኛ ውስጥ ደጎች አልሉ፡፡ ከኛም ከዚህ ሌላ የኾኑ አልሉ፡፡ የተለያዩ መንገዶች (ባለ ቤቶች) ነበርን፡፡
- 12. ‹እኛም አላህን በምድር ውስጥ ፈጽሞ የማናቅተው፤ ሸሽተንም ፈጽሞ የማናመልጠው መኾናችንን አረጋገጥን፡፡
- 13. ‹እኛም መሪውን በሰማን ጊዜ በርሱ አመንን፡፡ በጌታውም የሚያምን ሰው መግጎደልንም መጭጨመርንም አይፈራም፡፡
- 14. «እኛም ከእኛ ውስጥ ሙስሊሞች አልሉ፡፡ ከእኛም ውስጥ በዳዮች አልሉ፡፡ የሰለሙም ሰዎች እነዚያ ቅንን መንገድ መረጡ፡፡»
- 15. በዳዮቹማ ለገሀነም ማገዶ ኾኑ፡፡
- 16. እነሆም በመንገዲቱ ላይ ቀጥ ባሉ ኖሮ ብዙ ዝናምን ባጠጣናቸው ነበር (ማለትም ተወረደልኝ)፡፡
- 17. በእርሱ ልንሞክራቸው (ባጠጣናቸው ነበር)፡፡ ከጌታውም ማስታወሻ የሚያፈገፍግ ሰው አስቸጋሪን ቅጣት ያገባዋል፡፡
- 18. እነሆ መስጊዶችም የአላህ ብቻ ናቸው፡፡ (በውስጣቸው) ከአላህ ጋር አንድንም አትገዙ (ማለትም)፡፡
- 19. እነሆም የአላህ ባሪያ (ሙሐመድ አላህን) የሚጠራው ኾኖ በተነሳ ጊዜ (ጋኔኖች) በእርሱ ላይ ድርብርቦች ሊኾኑ ቀረቡ (ማለትም)፡፡
- 20. «እኔ የምግገዛው ጌታየን ብቻ ነው፡፡ በእርሱም አንድንም አላጋራም» በል፡፡
- 21. «እኔ ለእናንተ ጉዳትንም ቀጥታንም አልችልም» በላቸው፡፡
- 22. «እኔ ከአላህ (ቅጣት) አንድም አያድነኝም፡፡ ከእርሱም ሌላ መጠጊያን አላገኝም» በላቸው፡፡
- 23. «ከአላህ የኾነ ማድረስን መልክቶቹንም በስተቀር (አልችልም)፡፡ አላህንና መልክተኛውንም የሚያምጽ ሰው ለእርሱ የገሀነም እሳት አልለው፡፡ በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ፡፡»
- 24. የሚስፈራሩበትንም ባዩ ጊዜ ረዳቱ ደካማ፣ ቁጥሩም አነስተኛ የኾነው ማን እንደኾነ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡
- 25. «የምትስፈራሩበት ነገር ቅርብ ወይም ጌታየ ለእርሱ የተወሰነ ጊዜን የሚያደርግለት (ሩቅ) መኾኑን አላውቅም» በላቸው፡፡
- 26. «(እርሱ) ሩቁን ምስጢር ዐዋቂ ነው፡፡ በምስጢሩም ላይ አንድንም አያሳውቅም፡፡»
- 27. ከመልክተኛ ለወደደው ቢኾን እንጅ (ለሌላ አይገልጽም)፡፡ እርሱም ከስተፊቱም ከስተኋላውም ጠባቂዎችን ያደርግለታል፡፡
- 28. እነርሱ ዘንድ ባለው ነገር ዕውቀቱ የከበበና ነገሩንም ሁሉ በቁጥር ያጠቃለለ ሲኾን የጌታቸውን መልክቶች ያደረሱ መኾናቸውን ያውቅ ዘንድ (ጠባቂ ያደርጋል)፡፡