89. سورة الفجر - ቁርዓን
- 1. በጎህ እምላለሁ፡፡
- 2. በዐሥር ሌሊቶችም፡፡
- 3. በጥንዱም በነጠላውም፡፡
- 4. በሌሊቱም በሚኼድ ጊዜ፡፡
- 5. በዚህ (መሓላ) ለባለ አእምሮ ታላቅ መሓላ አለበትን?
- 6. ጌታህ በዓድ እንዴት እንደ ሠራ አታውቅምን?
- 7. በኢረም በባለ ረዣዢሚቱ አዕማድ፡፡
- 8. በዚያች ብጤዋ በአገሮች ውስጥ ያልተፈጠረ በኾነችው፡፡
- 9. በሰሙድም በእነዚያ በሸለቆው ቋጥኝን የቆረጡ በኾኑት፡፡
- 10. በፈርዖንም ባለ ችካሎች በኾነው፡፡
- 11. በእነዚያ በአገሮች ላይ ግፍ የሠሩ፡፡
- 12. በእርሷም ውስጥ ጥፋትን ያበዙ በኾኑት (እንዴት እንደሠራ አታውቅምን?)
- 13. በእነርሱ ላይም ጌታህ የቅጣትን አለንጋ አወረደባቸው፡፡
- 14. ጌታህ በመጠባበቂያ ላይ ነውና፡፡
- 15. ሰውማ ጌታው በሞከረው ጊዜ፣ ባከበረውና ባጣቀመውም (ጊዜ) «ጌታዬ አከበረኝ (አበለጠኝ)» ይላል፡፡
- 16. በሞከረውና በእርሱ ላይ ሲሳዩን ባጠበበ ጊዜማ «ጌታዬ አሳነሰኝ» ይላል፡፡
- 17. ይከልከል፤ ይልቁንም የቲምን አታከብሩም፡፡
- 18. ድኻንም በማብላት ላይ አትታዘዙም፡፡
- 19. የውርስንም ገንዘብ የመሰብሰብን አበላል ትበላላችሁ፡፡
- 20. ገንዘብንም ብዙን መውደድ ትወዳላችሁ፡፡
- 21. ተዉ፤ ምድር ደጋግማ በተሰባበረች ጊዜ፤
- 22. መላእክትም ሰልፍ ሰልፍ ኾነው ጌታህ (ትዕዛዙ) በመጣ ጊዜ፤
- 23. ገሀነምም በዚያ ቀን በተመጣች ጊዜ በዚያ ቀን ሰው (ጥፋቱን) ይገነዘባል፡፡ መገንዘብም ለእርሱ ከየቱ?
- 24. «ዋ እኔ! ምነው በሕይወቴ (መልካምን ሥራ) ባስቀደምኩ ኖሮ» ይላል፡፡
- 25. በዚያ ቀንም የርሱን አቀጣጥ አንድም አይቀጣም፡፡
- 26. የእርሱንም አስተሳሰር አንድም አያስርም፡፡
- 27. (ለአመነች ነፍስም) «አንቺ የረካሺው ነፍስ ሆይ!
- 28. «ወዳጅ ተወዳጅ ኾነሽ ወደ ጌታሽ ተመለሺ፡፡
- 29. «በባሮቼም ውስጥ ግቢ፡፡
- 30. ገነቴንም ግቢ፤» (ትባላለች)፡፡