50. سورة ق - ቁርዓን
- 1. ቀ (ቃፍ) በተከበረው ቁርኣን እምላለሁ (በሙሐመድ አላመኑም)፡፡
- 2. ይልቁንም ከነሱ ጎሳ የኾነ አስፈራሪ ስለ መጣላቸው ተደነቁ፡፡ ከሓዲዎቹም «ይህ አስደናቂ ነገር ነው» አሉ፡፡
- 3. «በሞትንና ዐፈር በኾን ጊዜ (እንመለሳለን?) ይህ ሩቅ የኾነ መመለስ ነው፤» (አሉ)፡፡
- 4. ከእነርሱ (አካል) ምድር የምታጎድለውን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ እኛም ዘንድ ጠባቂ መጽሐፍ አልለ፡፡
- 5. (አልተመለከቱም)፡፡ ይልቁንም በቁርኣን በመጣላቸው ጊዜ አስተባበሉ፡፡ እነርሱም በተማታ ነገር ውሰጥ ናቸው፡፡
- 6. ወደ ሰማይም ከበላያቸው ስትኾን ለእርሷ ምንም ቀዳዳዎች የሌሏት ኾና እንዴት እንደ ገነባናትና (በከዋክብት) እንዳጌጥናት አልተመለከቱምን?
- 7. ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት፡፡ በውስጧም ከሚያስደስት ዓይነት ሁሉ አበቀልን፡፡
- 8. (ይህንን ያደረግነው) ተመላሽ ለኾነ ባሪያ ሁሉ ለማሳየትና ለማስገንዘብ ነው፡፡
- 9. ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን፡፡ በእርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን (አዝመራ) ፍሬ አበቀልን፡፡
- 10. ዘምባባንም ረዣዢም ለእርሷ የተደራረበ እንቡጥ ያላት ስትኾን (አበቀልን)፡፡
- 11. ለባሮቹ ሲሳይ ትኾን ዘንድ (አዘጋጀናት)፡፡ በእርሱም የሞተችን አገር ሕያው አደረግንበት፡፡ (ከመቃብር) መውጣትም እንደዚሁ ነው፡፡
- 12. ከእነርሱ በፊት የኑሕ ሕዝቦችና የረሰስ ሰዎች፤ ሰሙድም አስተባበሉ፡፡
- 13. ዓድም ፈርዖንም፤ የሉጥ ወንድሞችም፤
- 14. የአይከት ሰዎችም የቱብበዕ ሕዝቦችም ሁሉም መልከተኞቹን አስተባበሉ፡፡ ዛቻዬም ተረጋገጠባቸው፡፡
- 15. በፊተኛው መፍጠር ደከምን? በእውነቱ እነርሱ ከአዲስ መፍጠር በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡
- 16. ሰውንም ነፍሱ (በሐሳቡ) የምታጫውተውን የምናውቅ ስንኾን በእርግጥ ፈጠርነው፤ እኛም ከደም ጋኑ ጅማት ይበልጥ ወደርሱ ቅርብ ነን፡፡
- 17. ሁለቱ ቃል ተቀባዮች (መላእክት) ከቀኝና ከግራ ተቀማጮች ኾነው በሚቀበሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
- 18. ከቃል ምንም አይናገርም በአጠገቡ ተጠባባቂና ዝግጁ የኾኑ (መላእክት) ያሉበት ቢኾን እንጅ፡፡
- 19. የሞትም መከራ እውነቱን ነገር ታመጣለች፡፡ (ሰው ሆይ)፡- «ይህ ያ ከርሱ ትሸሸው የነበርከው ነው» (ይባላል)፡፡
- 20. በቀንዱም ውስጥ ይንነፋል፡፡ ያ (ቀን) የዛቻው (መፈጸሚያ) ቀን ነው፡፡
- 21. ነፍስም ሁሉ ከእርሷ ጋር ነጂና መስካሪ ያለባት ኾና ትመጣለች፡፡
- 22. «ከዚህ ነገር በእርግጥ በዝንጋቴ ውስጥ ነበርክ፡፡ ሺፋንህንም ካንተ ላይ ገለጥንልህ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ዓይንህ ስለታም ነው» (ይባላል)፡፡
- 23. ቁራኛውም (መልአክ) «ይህ ያ እኔ ዘንድ ያለው ቀራቢ ነው» ይላል፡፡
- 24. «ሞገደኛ ከሓዲን ሁሉ በገሀነም ውስጥ ጣሉ፡፡»
- 25. «ለበጎ ሥራ ከልካይ፣ በዳይ፣ ተጠራጣሪ የኾነን ሁሉ፤» (ጣሉ)፡፡
- 26. «ያንን ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ ያደረገውን በብርቱ ቅጣት ውስጥ ጣሉት፤» (ይባላል)፡፡
- 27. ቁራኛው (ሰይጣን) «ጌታችን ሆይ! እኔ አላሳሳትኩትም፡፡ ግን (ራሱ) በሩቅ ስሕተት ውስጥ ነበር» ይላል፡፡
- 28. (አላህ) «ወደእናንተ ዛቻን በእርግጥ ያስቀደምኩ ስኾን እኔ ዘንድ አትጨቃጨቁ» ይላቸዋል፡፡
- 29. «ቃሉ እኔ ዘንድ አይለወጥም፡፡ እኔም ለባሮቼ ፈጽሞ በዳይ አይደለሁም» (ይላቸዋል)፡፡
- 30. ለገሀነም «ሞላሽን? የምንልበትንና ጭማሪ አለን? የምትልበትን ቀን» (አስጠንቅቃቸው)፡፡
- 31. ገነትም አላህን ለፈሩት እሩቅ ባልኾነ ስፍራ ትቅቀረባለች፡፡
- 32. «ይህ ወደ አላህ ተመላሽና (ሕግጋቱን) ጠባቂ ለኾነ ሁሉ የተቀጠራችሁት ነው» (ይባላሉ)፡፡
- 33. «አልረሕማንን በሩቁ ኾኖ ለፈራና በንጹሕ ልብ ለመጣ» (ትቅቀረባለች)፡፡
- 34. «በሰላም ግቧት ይህ የመዘውተሪያ ቀን ነው» (ይባላሉ)፡፡
- 35. ለነርሱ በውስጧ ሲኾኑ የሚሹት ሁሉ አልላቸው፡፡ እኛም ዘንድ ጭማሪ አልለ፡፡
- 36. ከእነርሱም (ከቁረይሾች) በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን እነርሱ በኀያልነት ከእነርሱ ይበልጥ የበረቱ የኾኑትን (ማምለጫ ፍለጋ) በየአገሮቹም የመረመሩትን አጥፍተናል፡፡ ማምለጫ አለን?
- 37. በዚህ ውሰጥ ለእርሱ ልብ ላለው ወይም እርሱ (በልቡ) የተጣደ ኾኖ (ወደሚነበብለት) ጆሮውን ለጣለ ሰው ግሳጼ አለበት፡፡
- 38. ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ድካምም ምንም አልነካንም፡፡
- 39. በሚሉትም ላይ ታገሥ፤ ጌታህንም ከማመስገን ጋር ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ከመግባቷም በፊት አወድሰው፡፡
- 40. ከሌሊቱም አወድሰው ከስግደቶችም በኋላዎች (አወድሰው)፡፡
- 41. (የሚነገርህን) አዳምጥም፡፡ ጠሪው ከቅርብ ስፍራ በሚጠራበት ቀን (ከመቃብራቸው ይወጣሉ)፡፡
- 42. ጩኸቲቱን በእውነት የሚሰሙበት ቀን ያ (ከመቃብር) የመውጫው ቀን ነው፡፡
- 43. እኛ እኛው ሕያው እናደርጋለን፡፡ እንገድላለንም፡፡ መመለሻም ወደእኛ ብቻ ነው፡፡
- 44. የሚፈጥኑ ኾነው ምድር ከእነርሱ ላይ የምትሰነጣጠቅበት ቀን (የመውጫው ቀን ነው)፡፡ ይህ በእኛ ላይ ገር የኾነ መሰብሰብ ነው፡፡
- 45. እኛ የሚሉትን ሁሉ ዐዋቂ ነን፡፡ አንተም በእነርሱ ላይ አስገዳጅ አይደለህም፡፡ ስለዚህ ዛቻየን የሚፈራን ሰው በቁርኣን አስታውስ፡፡