70. سورة المعارج - ቁርዓን
- 1. ወዳቂ ከኾነው ቅጣት ጠያቂ ጠየቀ፡፡
- 2. በከሓዲዎች ላይ (ወዳቂ ከኾነው) ለእርሱ መላሽ የለውም፡፡
- 3. የ(ሰማያት) መሰላሎች ባለቤት ከኾነው አላህ (መላሽ የለውም)፡፡
- 4. መላእክቱና መንፈሱም ልኩ አምሳ ሺሕ ዓመት በኾነ ቀን ውስጥ ወደእርሱ ያርጋሉ፤ (ይወጣሉ)፡፡
- 5. መልካምንም ትዕግስት ታገሥ፡፡
- 6. እነርሱ (ያንን ቀን) ሩቅ አድርገው ያዩታል፡፡
- 7. እኛም ቅርብ ኾኖ እናየዋለን፡፡
- 8. ሰማይ እንደ ዘይት አተላ በምትኾንበት ቀን፡፡
- 9. ጋራዎችም በተለያዩ ቀለማት እንደ ተነከረ ሱፍ (ነፋስ እንደሚያበረው) በሚኾኑበት ቀን፡፡
- 10. ዘመድም ዘመድን በማይጠይቅበት ቀን፤ (መላሽ የለውም)፡፡
- 11. (ዘመዶቻቸውን) ያዩዋቸዋል፡፡ አመጸኛው ከዚያ ቀን ስቃይ (ነፍሱን) በልጆቹ ሊበዥ ይመኛል፡፡
- 12. በሚስቱም በወንድሙም፡፡
- 13. በዚያችም በምታስጠጋው ጎሳው፡፡
- 14. በምድርም ላይ ባለው ሁሉ (ሊበዥ) ከዚያም ሊያድነው (ይመኛል)፡፡
- 15. ይተው! እርሷ (እሳቲቱ) ለዟ ናት፡፡
- 16. የራስን ቅል ቆዳ የምትሞሽልቅ ስትኾን፡፡
- 17. (ከእምነት) የዞረንና የሸሸን ሰው (ወደእርሷ) ትጠራለች፡፡
- 18. ገንዘብን የሰበሰበንና (ዘካውን ሳይሰጥ) የቆጠረንም፤ (ትጠራለች)፡፡
- 19. ሰው ቅጠ ቢስ ኾኖ ተፈጠረ፡፡
- 20. ክፉ ነገር ባገኘው ጊዜ ብስጪተኛ፡፡
- 21. መልካምም ነገር (ድሎት) ባገኘ ጊዜ ከልካይ (ኾኖ ተፈጠረ)፡፡
- 22. ሰጋጆቹ ብቻ ሲቀሩ፡፡
- 23. እነዚያ እነርሱ በስግደታቸው ላይ ዘውታሪዎች የኾኑት፡፡
- 24. እነዚያም በገንዘቦቻቸው ላይ የታወቀ መብት ያለባቸው የኾኑት፡፡
- 25. ለለማኝ ከልመና ለሚከለከልም (መብት ያለባቸው የኾኑት)፡፡
- 26. እነዚያም በፍርዱ ቀን እውነት የሚሉት (የሚያረጋግጡት)፡፡
- 27. እነዚያም እነርሱ ከጌታቸው ቅጣት ፈሪዎች የኾኑት፡፡
- 28. የጌታቸው ቅጣት (መምጣቱ) የማያስተማምን ነውና፡፡
- 29. እነዚያም እነርሱ ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች የኾኑት፡፡
- 30. በሚስቶቻቸው ወይም እጆቻቸው በያዙዋቸው (ባሪያዎች) ላይ ሲቀር፡፡ እነርሱ (በእነዚህ) የማይወቀሱ ናቸውና፡፡
- 31. ከዚያም ወዲያ የፈለገ ሰው እነዚያ እነሱ ድንበር አላፊዎች ናቸው፡፡
- 32. እነዚያም እነርሱ አደራዎቻቸውንና ቃል ኪዳናቸውን ጠባቂዎች የኾኑት፡፡
- 33. እነዚያም እነርሱ በምስክርነታቸው ትክክለኞች የኾኑት፡፡
- 34. እነዚያም እነርሱ በሶላቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁት፡፡
- 35. እነዚህ (ከዚህ በላይ የተወሱት ሁሉ) በገነቶች ውስጥ የሚከበሩ ናቸው፡፡
- 36. ለእነዚያም ለካዱት ወደ አንተ በኩል አንገቶቻቸውን መዝዘው የሚያተኩሩት ምን አላቸው?
- 37. ከቀኝና ከግራ ክፍልፍል ጭፍሮች ሲኾኑ፡፡
- 38. ከእነርሱ እያንዳንዱ ሰው የጸጋይቱን ገነት መግባትን ይከጅላልን?
- 39. ይከልከል፤ እኛ ከሚያውቁት ነገር (ከፍቶት ጠብታ) ፈጠርናቸው፡፡
- 40. በምሥራቆችና በምዕራቦችም ጌታ እምላለሁ፡፡ እኛ በእርግጥ ቻዮች ነን፡፡
- 41. ከእነርሱ የተሻለን በመለወጥ ላይ፡፡ እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም፡፡
- 42. ያንንም የሚስፈራሩበትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው፡፡ ይዋኙ ይጫወቱም፡፡
- 43. ወደ ጣዖቶች እንደሚሽቀዳደሙ ኾነው ከመቃብሮቻቸው ፈጥነው የሚወጡበትን ቀን (እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው)፡፡
- 44. ዓይኖቻቸው ያፈሩ ኾነው ውርደት ትሸፍናቸዋለች፡፡ ይህ ቀን ያ ይስፈራሩበት የነበሩት ነው፡፡