56. سورة الواقعة - ቁርዓን
- 1. መከራይቱ በወደቀች ጊዜ፡፡
- 2. ለመውደቋ አስተባባይ (ነፍስ) የለችም፡፡
- 3. ዝቅ አድራጊና ከፍ አድራጊ ናት፡፡
- 4. ምድር መናወጥን በተናወጠች ጊዜ፡፡
- 5. ተራራዎችም መፍፈርፈርን በተፈረፈሩ ጊዜ (እንደተፈጨ ዱቄት በኾኑ ጊዜ)፡፡
- 6. የተበተነ ብናኝ በኾኑም ጊዜ
- 7. ሦስት ዓይነቶችም በኾናችሁ ጊዜ (ታዋርዳለች፤ ታነሳለችም)፡፡
- 8. የቀኝ ጓዶችም ምን (የተከበሩ) የቀኝ ጓዶች ናቸው፡፡
- 9. የግራ ጓዶችም ምን (የተዋረዱ) የግራ ጓዶች ናቸው፡፡
- 10. (ለበጎ ሥራ) ቀዳሚዎቹም (ለገነት) ቀዳሚዎች ናቸው፡፡
- 11. እነዚያ ባለሟሎቹ ናቸው፡፡
- 12. በመጠቀሚያ ገነቶች ውስጥ ሲኾኑ፡፡
- 13. ከፊተኞቹ ብዙ ጭፍሮች ናቸው፡፡
- 14. ከኋለኞቹም ጥቂቶች ናቸው፡፡
- 15. በተታቱ አልጋዎች ላይ ይኾናሉ፡፡
- 16. በእርሷ ላይ የተመቻቹና ፊት ለፊት የተቅጣጩ ሲኾኑ፡፡
- 17. በእነርሱ ላይ ሁል ጊዜ የማያረጁ ወጣቶች ልጆች ይዘዋወራሉ፡፡
- 18. ከጠጅ ምንጭም በብርጭቆዎችና በኩስኩስቶች በጽዋም (በእነርሱ ላይ ይዝዞራሉ)፡፡
- 19. ከእርሷ የራስ ምታት አያገኛቸውም፤ አይሰክሩምም፡፡
- 20. ከሚመርጡትም ዓይነት በእሸቶች፡፡
- 21. ከሚሹትም በኾነ የበራሪ ሥጋ (ይዞሩባቸዋል)፡፡
- 22. ዓይናማዎች የኾኑ ነጫጭ ቆንጆዎችም አሏቸው፡፡
- 23. ልክ እንደተሸፈነ ሉል መሰሎች የኾኑ፡፡
- 24. በዚያ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ዋጋ ይኾን ዘንድ (ይህንን አደረግንላቸው)፡፡
- 25. በውስጥዋ ውድቅ ንግግርንና መውወንጀልን አይሰሙም፡፡
- 26. ግን ሰላም መባባልን (ይሰማሉ)፡፡
- 27. የቀኝም ጓዶች ምንኛ (የከበሩ) የቀኝ ጓዶች!
- 28. በተቀፈቀፈ (እሾህ በሌለው) ቁርቁራ ውስጥ ናቸው፡፡
- 29. (ፍሬው) በተነባበረ በሙዝ ዛፍም፡፡
- 30. በተዘረጋ ጥላ ሥርም፡፡
- 31. በሚንቧቧ ውሃ አጠገብም፡፡
- 32. ብዙ (ዓይነት) በኾኑ ፍራፍሬዎችም፡፡
- 33. የማትቋረጥም የማትከለከልም የኾነች፡፡
- 34. ከፍ በተደረጉ ምንጣፎችም (ሴቶችም መካከል)፡፡
- 35. እኛ አዲስ ፍጥረት አድርገን (ለእነርሱ) ፈጠርናቸው፡፡
- 36. ደናግሎችም አደረግናቸው፡፡
- 37. ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎች እኩያዎች (አደረግናቸው)፡፡
- 38. ለቀኝ ጓዶች (አዘጋጀናቸው)፡፡
- 39. ከፊተኞቹ ብዙ ጭፍሮች ናቸው፡፡
- 40. ከኋለኞቹም ብዙ ጭፍሮች ናቸው፡፡
- 41. የግራ ጓደኞችም ምንኛ (የተዋረዱ) የግራ ጓዶች! ናቸው፡፡
- 42. በመርዛም ነፋስ በጣም በፈላ ውሃም ውስጥ ናቸው፡፡
- 43. ከጥቁር ጭስም በኾነ ጥላ ውስጥ፡፡
- 44. ቀዝቃዛም መልካምም ያልኾነ፡፡
- 45. እነርሱ ከዚህ በፊት ቅምጥሎች ነበሩና፡፡
- 46. በታላቅ ኀጢአትም ላይ ይዘወትሩ ነበሩና፡፡
- 47. ይሉም ነበሩ፡- «በሞትንና ዐፈር፣ ዐጥንቶችም በኾን ጊዜ እኛ በእርግጥ የምንቀሰቀስ ነን?
- 48. «የፊተኞቹ አባቶቻችንም?»
- 49. በላቸው፡- «ፊተኞቹም ኋለኞቹም፡፡
- 50. «በተወሰነ ቀን ቀጠሮ በእርግጥ ተሰብሳቢዎች ናቸው፡፡
- 51. «ከዚያም እናንተ ጠማሞች አስተባባዮች ሆይ!
- 52. « ከዘቁም ዛፍ በእርግጥ በይዎች ናችሁ፡፡
- 53. «ከእርሷም ሆዶቻችሁን ሞይዎች ናችሁ፡፡
- 54. «በእርሱ ላይም ከፈላ ውሃ ጠጪዎች ናችሁ፡፡
- 55. «የተጠሙንም ግመሎች አጠጣጥ ብጤ ጠጪዎች ናችሁ፡፡»
- 56. ይህ በፍርዱ ቀን መስተንግዷቸው ነው፡፡
- 57. እኛ ፈጠርናችሁ አታምኑምን?
- 58. (በማኅፀኖች) የምታፈሱትን አያችሁን?
- 59. እናንተ ትፈጥሩታላችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎቹን ነን?
- 60. እኛ ሞትን (ጊዜውን) በመካከላችሁ ወሰንን፡፡ እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም፡፡
- 61. ብጤዎቻችሁን በመለወጥና በዚያ በማታውቁትም (ቅርጽ) እናንተን በመፍጠር ላይ (አንሸነፍም)፡፡
- 62. የፊተኛይቱንም አፈጣጠር በእርግጥ ዐውቃችኋል፡፡ አትገነዘቡምን?
- 63. የምትዘሩትንም አያችሁን?
- 64. እናንተ ታበቅሉታላችሁን? ወይስ እኛ አብቃዮቹ ነን?
- 65. ብነሻ ኖሮ ደረቅ ስብርብር ባደረግነውና የምትደነቁም በኾናችሁ ነበር፡፡
- 66. «እኛ በዕዳ ተያዦች ነን፡፡
- 67. «በእርግጥም እኛ (ከመጠቀም) የተከለከልን ነን» (ትሉ ነበር)፡፡
- 68. ያንንም የምትጠጡትን ውሃ አየችሁን?
- 69. እናንተ ከደመናው አወረዳችሁትን? ወይስ እኛ አውራጆቹ ነን?
- 70. ብንሻ ኖሮ መርጋጋ ባደረግነው ነበር፡፡ አታመሰግኑምን?
- 71. ያቺንም የምትሰብቋትን እሳት አያችሁን?
- 72. እናንተ ዛፏን ፈጠራችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎችዋ ነን?
- 73. እኛ (ለገሀናም) ማስታወሻ ለመንገደኞችም መጠቀሚያ አደረግናት፡፡
- 74. የታላቁን ጌታህንም ስም አወድስ፡፡
- 75. በከዋክብትም መጥለቂያዎች እምላለሁ፡፡
- 76. እርሱም ብታወቁ ታላቅ መሓላ ነው፡፡
- 77. እርሱ የከበረ ቁርኣን ነው፡፡
- 78. በተጠበቀ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡
- 79. የተጥራሩት እንጅ ሌላ አይነካውም፡፡
- 80. ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡
- 81. በዚህ ንግግር እናንተ ቸልተኞች ናችሁን?
- 82. ሲሳያችሁንም (ዝናምን) እናንተ የምታስተባብሉት ታደርጋላችሁን?
- 83. (ነፍስ) ጉረሮንም በደረሰች ጊዜ፡፡
- 84. እናንተ ያን ጊዜ የምታዩ ስትኾኑ፡፡
- 85. እኛም ግን አታዩም እንጅ ከእናንተ ይልቅ ወደእርሱ የቀረብን ስንኾን፡፡
- 86. የማትዳኙም ከኾናችሁ፡፡
- 87. እውነተኞች እንደ ኾናችሁ (ነፍሲቱን ወደ አካሉ) ለምን አትመልሷትም፡፡
- 88. (ሟቹ) ከባለሟሎቹ ቢኾንማ፡፡
- 89. (ለእርሱ) ዕረፍት፣ መልካም ሲሳይም፣ የመጠቀሚያ ገነትም አልለው፡፡
- 90. ከቀኝ ጓዶችም ቢኾንማ፡፡
- 91. ከቀኝ ጓዶች ስለ ኾንክ ላንተ ሰላም አልለህ (ይባላል)፡፡
- 92. ከሚያስዋሹት ጠማማዎችም ቢኾንማ፡፡
- 93. ከፈላ ውሃ የኾነ መስተንግዶ አልለው፡፡
- 94. በገሀነም መቃጠልም (አልለው)፡፡
- 95. ይህ እርሱ እርግጠኛ እውነት ነው፡፡
- 96. የታላቁንም ጌታህን ስም አወድስ፡፡