25. سورة الفرقان - ቁርዓን
- 1. ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብርና ጥራት ተገባው፡፡
- 2. (እርሱ) ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና የእርሱ ብቻ የኾነ፣ ልጅንም ያልያዘ፣ በንግሥናውም ተጋሪ የሌለው፣ ነገሩንም ሁሉ የፈጠረና በትክክልም ያዘጋጀው ነው፡፡
- 3. (ከሓዲዎች) ከእርሱም ሌላ ምንንም የማይፈጥሩን፣ እነርሱም የሚፈጠሩን፣ ለነፍሶቻቸውም ጉዳትን ለመከላከል ጥቅምንም ለማምጣት የማይችሉን ሞትንና ሕይወትንም መቀስቀስንም የማይችሉን፣ አማልክት ያዙ፡፡
- 4. እነዚያም የካዱት ይህ (ቁርኣን ሙሐመድ) የቀጠፈው በእርሱም ላይ ሌሎች ሕዝቦች ያገዙት የኾነ ውሸት እንጂ ሌላ አይደለም አሉ፡፡ በእርግጥም በደልንና እብለትን ሠሩ፡፡
- 5. አሉም «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናት፡፡ አስጻፋት፡፡ እርሷም በእርሱ ላይ ጧትና ማታ ትነበብለታለች፡፡»
- 6. «ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው፡፡ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡
- 7. ለዚህም መልክተኛ ምግብን የሚበላ፣ በገበያዎችም የሚኼድ ሲኾን ምን (መልክተኛነት) አለው ከርሱ ጋር አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ወደርሱ መልአክ (ገሃድ) አይወረድም ኖሯልን አሉ፡፡
- 8. «ወይም ወደእርሱ ድልብ አይጣልለትምን ወይም ከእርሷ የሚበላላት አትክልት ለእርሱ አትኖረውምን» (አሉ)፡፡ በዳዮቹም (ላመኑት) «የተደገመበትን ሰው እንጂ ሌላ አትከተሉም» አሉ፡፡
- 9. ላንተ ምሳሌዎችን እንዴት እንዳደረጉልህና እንደተሳሳቱ ተመልከት፡፡ (ወደ እውነት ለመድረስ) መንገድንም አይችሉም፡፡
- 10. ያ ቢሻ ከዚህ (ካሉት) የተሻለን ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን አትክልቶች ላንተ የሚያደርግልህ ሕንጻ ቤቶችንም ላንተ የሚያደርግልህ ጌታ ችሮታው በዛ፡፡
- 11. ይልቁንም በትንሣኤ አስተባበሉ፡፡ በትንሣኤ ላስተባበለም ሰው ሁሉ ነዳጅን እሳት አዘጋጅተናል፡፡
- 12. ከሩቅ ስፍራ ባየቻቸው ጊዜ ለእርሷ የቁጭት መገንፈልንና ማናፋትን ይሰማሉ፡፡
- 13. እጅ ከፍንጅ የታሠሩ ኾነውም ከእርሷ በጠባብ ስፍራ በተጣሉ ጊዜ በዚያ ስፍራ ጥፋትን ይጠራሉ፤ (ዋ ጥፋታችን ይላሉ)፡፡
- 14. ፡-ዛሬ አንድን ጥፋት ብቻ አትጥሩ ብዙንም ጥፋት ጥሩ (ይባላሉ)፡፡
- 15. (እንዲህ) በላቸው «ይህ የተሻለ ነውን ወይስ ጥንቁቆቹ ተስፋ የተሰጧት የዘለዓለሟ ገነት» ለእነርሱ ምንዳና መመለሻ ኾነች፡፡
- 16. ለእነሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ኾነው የሚፈልጉት ሁሉ አልላቸው፡፡ (ይህም) ተስፋ ከጌታህ ተለማኝ ተስፋ ነው፡፡
- 17. እነርሱንና ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸውንም የሚሰበስብባቸውንና «እናንተ እነዚህን ባሮቼን አሳሳታችሁን ወይስ እነሱው መንገድን ሳቱ» የሚልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡
- 18. «ጥራት ይገባህ፤ ካንተ ሌላ ረዳቶችን ልንይዝ ለእኛ ተገቢያችን አልነበረም፡፡ ግን እነርሱንም አባቶቻቸውንም መገንዘብን እስከተዉ ድረስ አጣቀምካቸው፡፡ ጠፊ ሕዝቦችም ኾኑ» ይላሉ፡፡
- 19. በምትሉትም (አማልክቶቻችሁ) አስዋሹዋችሁ፡፡ ቅጣቴን መገፍተርንም መርዳትንም አትችሉም፡፡ ከእናንተም የሚበድለውን ታላቅን ቅጣት እናቀምሰዋለን፤ (ይባላሉ)፡፡
- 20. ከአንተ በፊትም ከመልክተኞች እነሱ በእርግጥ ምግብን የሚበሉ በገበያዎችም የሚኼዱ ኾነው በስተቀር አልላክንም፡፡ ከፊላችሁንም ለከፊሉ ፈተና አድርገናል፡፡ ትታገሳላችሁን ጌታህም ተመልካች ነው፡፡
- 21. እነዚያም መገናኘታችንን የማይፈሩት በእኛ ላይ ለምን መላእክት አልወረደም፡፡ ወይም ጌታችንን ለምን አናይም አሉ፡ በነፍሶቻቸው ውስጥ በእርግጥ ኮሩ፡፡ ታላቅንም አመጽ አመፁ፡፡
- 22. መላእክትን በሚያዩበት ቀን በዚያ ጊዜ ለአመጸኞች ምስራች የላቸውም፡፡ «የተከለከለ ክልክልም አድርገን» ይላሉ፡፡
- 23. ከሥራም ወደ ሠሩት እናስባለን፡፡ የተበተነ ትቢያም እናደርገዋለን፡፡
- 24. የገነት ሰዎች በዚያ ቀን በመርጊያ የተሻሉ በማረፊያም በጣም ያማሩ ናቸው፡፡
- 25. ሰማይም በደመና የምትቀደድበትንና መላእክትም መወረድን የሚወርድበትን ቀን (አስታውስ)፡፡
- 26. እውነተኛው ንግሥና በዚያ ቀን ለአልራሕማን ብቻ ነው፡፡ በከሓዲዎችም ላይ አስቸጋሪ ቀን ነው፡፡
- 27. በዳይም «ከመልክተኛው ጋር ቀጥተኛን መንገድ ይዤ በኾነ ዋ ምኞቴ!» እያለ (በጸጸት) ሁለት እጆቹን የሚነክስበትን ቀን (አስታውስ)፡፡
- 28. «ዋ ጥፋቴ! እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ፡፡
- 29. (የእምነት ቃልን) ከመጣልኝ በኋላ ከማስታወስ በእርግጥ አሳሳተኝ» (ይላል)፡፡ ሰይጣንም ለሰው አጋላጭ ነው፡፡
- 30. መልክተኛውም «ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ ይህንን ቁርኣን የተተወ ነገር አድርገው ያዙት» አለ፡፡
- 31. እንደዚሁም ለነቢዩ ሁሉ ከአመጸኞች የኾነ ጠላትን አድርገናል፡፡ መሪና ረዳትም በጌታህ በቃ፡፡
- 32. እነዚያ የካዱትም «ቁርኣን በእርሱ ላይ ለምን በጠቅላላ አንድ ጊዜ አልተወረደም» አሉ፡፡ እንደዚሁ በእርሱ ልብህን ልናረጋ (ከፋፍለን አወረድነው)፡፡ ቀስ በቀስ መለያየትንም ለየነው፡፡
- 33. በጥያቄም አይመጡብህም እውነተኛውን (መልስ) መልካምን ፍችም የምናመጣልህ ብንኾን እንጅ፡፡
- 34. እነዚያ በፊቶቻቸው ለይ (እየተጎተቱ) ወደ ገሀነም የሚሰበሰቡ ናቸው፡፡ እነዚያ ስፍራቸው የከፋ መንገዳቸውም የጠመመ ናቸው፡፡
- 35. በእርግጥም ለሙሳ መጽሐፍን ሰጠነው፡፡ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ሃሩንን ረዳት አደረግንለት፡፡
- 36. «ወደእነዚያም በተዓምራቶቻችን ወደ አስተባበሉት ሕዝቦች ኺዱ» አልናቸው፡፡ (አስዋሿቸውም) ማጥፋትንም አጠፋናቸው፡፡
- 37. የኑሕን ሰዎችም መልክተኞችን ባስተባበሉ ጊዜ አሰጠምናቸው፡፡ ለሰዎችም መገሰጫ አደረግናለቸው፡፡ ለበደለኞችም አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
- 38. ዓድንም ሰሙድንም የረስን ሰዎችም በዚህ መካከል የነበሩትንም ብዙን የክፍለ ዘመናት ሕዝቦች (አጠፋን)፡፡
- 39. ሁሉንም (ገሠጽን) ለእነሱ ምሳሌዎችን ገለጽን፡፡ ሁሉንም ማጥፋትን አጠፋናቸውም፡፡
- 40. በዚያችም ክፉ ዝናምን በተዘነመችው ከተማ ላይ (የመካ ከሐዲዎች) በእርግጥ መጥተዋል፡፡ የሚያዩዋት አልነበሩምን በእውነቱ መቀስቀስን የማይፈሩ ነበሩ፡፡
- 41. ባዩህም ጊዜ ያ አላህ መልእክተኛ አድርጎ የላከው ይህ ነውን እያሉ መሳለቂያ እንጂ ሌላ አያደርጉህም፡፡
- 42. «እነሆ በእርሷ ላይ መታገሳችን ባልነበረ ኖሮ ከአማልክቶቻችን ሊያሳስተን ቀርቦ ነበር» (ሲሉም ይሳለቃሉ)፡፡ ወደፊትም ቅጣቱን በሚያዩ ጊዜ መንገድን በጣም ተሰሳቹ ማን እንደኾነ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡
- 43. ፍላጎቱን አምላኩ አድርጎ የያዘውን ሰው አየህን አንተ በእርሱ ላይ ጠባቂ ትኾናለህን
- 44. ይልቁንም አብዛኛዎቻቸው የሚሰሙ ወይም የሚያውቁ መኾናቸውን ታስባለህን እነርሱ እንደ እንስሳዎች እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ከቶውንም እነሱ ይልቅ መንገድን የተሳሳቱ ናቸው፡፡
- 45. ወደ ጌታህ (ሥራ) ጥላን እንዴት እንደ ዘረጋ አላየህምን በሻም ኖሮ የረጋ ባደረገው ነበር፡፡ ከዚያም ፀሐይን በእርሱ ላይ ምልክት አደረግን፡፡
- 46. ከዚያም ቀስ በቀስ ወደእኛ ሰብሰብነው፡፡
- 47. እርሱም ያ ለእናንተ ሌሊትን ልብስ እንቅልፍንም ማረፊያ ያደረገ፤ ቀንንም መበተኛ ያደረገላችሁ ነው፡፡
- 48. እርሱም ያ ነፋሶችን አብሳሪዎች ሲኾኑ ከዝናሙ በስተፊት የላከ ነው፡፡ ከሰማይም አጥሪ ውሃን አወረድን፡፡
- 49. በእርሱ የሞተችን አገር ሕያው ልናደርግበት ከፈጠርነውም ፍጡር እንስሳዎችንና ብዙ ሰዎችንም ልናጠጣው (አወረድነው)፡፡
- 50. (ጸጋችንን) ይገነዘቡም ዘንድ በመካከላቸው ከፋፈልነው፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች ክህደትን እንጂ እንቢ አሉ፡፡
- 51. በሻንም ኖሮ በየከተማይቱ አስፈራሪን በላክን ነበር፡፡
- 52. ከሓዲዎችንም አትታዘዛቸው፡፡ በእርሱም (በቁርኣን) ታላቅን ትግል ታገላቸው፡፡
- 53. እርሱም ያ ሁለቱን ባሕሮች አጎራብቶ የለቀቀ ነው፡፡ ይህ ጥምን የሚቆርጥ ጣፋጭ ነው፡፡ ይህም የሚመረግግ ጨው ነው፡፡ በመካከላቸውም (ከመቀላቀል) መለያንና የተከለለን ክልል ያደረገ ነው፡፡
- 54. እርሱም ያ ከውሃ ሰውን የፈጠረ፣ የዝምድናና የአማችም ባለቤት ያደረገው ነው፡፡ ጌታህም ቻይ ነው፡፡
- 55. ከአላህም ሌላ የማይጠቅማቸውንና የማይጎዳቸውን ይግገዛሉ፤ ከሓዲም በጌታው ላይ (በማመጽ ለሰይጣን) ረዳት ነው፡፡
- 56. አብሳሪና አስፈራሪም አድርገን እንጂ አልላክንህም፡፡
- 57. «በእርሱ ላይ ዋጋን በፍጹም አልጠይቃችሁም፡፡ ግን ወደ ጌታው (መልካም) መንገድን ለመያዝ የሻ ሰው (ይሥራ)» በላቸው፡፡
- 58. በዚያም በማይሞተው ሕያው አምላክ ላይ ተመካ፡፡ ከማመስገንም ጋር አጥራው፡፡ በባሮቹ ኀጢኣቶችም ውስጠ ዐዋቂ በእርሱ በቃ፡፡
- 59. ያ ሰማያትና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ፣ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ሥልጣኑ) የተደላደለ አልረሕማን ነው፡፡ ከእርሱም ዐዋቂን ጠይቅ፡፡
- 60. ለእነርሱም ለአልረሕማን ስገዱ በተባሉ ጊዜ አልረሕማን ማነው ለምታዘን (እና ለማናውቀው) እንሰግዳለን ይላሉ፡፡ (ይህ) መራቅንም ጨመራቸው፡፡
- 61. ያ በሰማይ ቡሩጆችን ያደረገና በእርሷም አንጸባራቂን (ፀሐይ) አብሪ ጨረቃንም ያደረገ ጌታ ክብሩ በጣም ላቀ፡፡
- 62. እርሱም ያ (ያመለጠውን ሥራ) ማስታወስን ለሚፈልግ ወይም ማመስገንን ለሚፈልግ ሰው ሌሊትንና ቀንን ተተካኪ ያደረገ ነው፡፡
- 63. የአልረሕማንም ባሮች እነዚያ በምድር ላይ በዝግታ የሚኼዱት፣ ባለጌዎችም (በክፉ) ባነጋገሩዋቸው ጊዜ ሰላም የሚሉት ናቸው፡፡
- 64. እነዚያም ለጌታቸው በግንባራቸው ተደፊዎችና ቋሚዎች ኾነው የሚያድሩት ናቸው፡፡
- 65. እነዚያም «ጌታችን ሆይ! የገሀነምን ቅጣት ከእኛ ላይ መልስልን ቅጣቷ የማይለቅ ነውና» የሚሉት ናቸው፡፡
- 66. እርሷ መርጊያና መቀመጫ በመኾን ከፋች! (ይላሉ)፡፡
- 67. እነዚያም በለገሱ ጊዜ የማያባክኑ የማይቆጥቡትም ናቸው፡፡ በዚህም መካከል (ልግስናቸው) ትክክለኛ የኾነ ነው፡፡
- 68. እነዚያም ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ የማይገዙት፣ ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ ያለ ሕግ የማይገድሉት፣ የማያመነዝሩትም ናቸው፡፡ ይህንንም የሚሠራ ሰው ቅጣትን ያገኛል፡፡
- 69. በትንሣኤ ቀን ቅጣቱ ለእርሱ ይደራረባል፡፡ በእርሱም ውስጥ የተዋረደ ኾኖ ይኖራል፡፡
- 70. ተጸጽቶ የተመለሰና ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡ እነዚያም አላህ መጥፎ ሥራዎቻቸውን በመልካም ሥራዎች ይለውጣል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
- 71. ተጸጽቶ የተመለሰም ሰው መልካምንም የሠራ እርሱ የተወደደን መመለስ ወደ አላህ ይመለሳል፡፡
- 72. እነዚያም እብለትን የማይመሰክሩ፤ በውድቅ ቃልም (ተናጋሪ አጠገብ) ባለፉ ጊዜ የከበሩ ኾነው የሚያልፉት ናቸው፡፡
- 73. እነዚያም በጌታቸው አንቀጾች በተገሰጹ ጊዜ (የተረዱ ተቀባዮች ኾነው እንጂ) ደንቆሮዎችና ዕውሮች ኾነው በእርሷ ላይ የማይደፉት ናቸው፡፡
- 74. እነዚያም «ጌታችን ሆይ! ከሚስቶቻችንና ከዘሮቻችን ለዓይኖች መርጊያን ለእኛ ስጠን፡፡ አላህን ለሚፈሩትም መሪ አድርገን» የሚሉት ናቸው፡፡
- 75. እነዚያ በመታገሳቸው የገነትን ሰገነቶች ይምመነዳሉ፡፡ በእርሷም ውስጥ ውዳሴንና ሰላምታን ይስሰጣሉ፡፡
- 76. በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ኾነው (ይስሰጣሉ)፡፡ መርጊያና መኖሪያይቱ አማረች፡፡
- 77. «ጸሎታችሁ ባልነበረ ኖሮ ጌታዬ እናንተን ከምንም አይቆጥራችሁም ነበር፡፡ በእርግጥም አስተባበላችሁ፤ ወደ ፊትም (ቅጣቱ) ያዣችሁ ይኾናል» በላቸው፡፡