21. سورة الأنبياء - ቁርዓን
- 1. ለሰዎች እነርሱ በዝንጋቴ ውስጥ (መሰናዳትን) የተው ኾነው ሳሉ ምርመራቸው ቀረበ፡፡
- 2. ከጌታቸው አዲስ የተወረደ ቁርኣን አይመጣላቸውም፡፡ እነሱ የሚያላግጡ ሆነው የሚያደምጡት ቢሆኑ እንጂ፡፡
- 3. ልቦቻቸው ዝንጉዎች ኾነው (የሚያዳምጡት ቢኾኑ እንጅ)፡፡ እነዚያም የበደሉት ሰዎች መንሾካሾክን ደበቁ፡፡ «ይህ ብጤያችሁ ሰው እንጅ ሌላ ነውን እናንተም የምታዩ ስትኾኑ ድግምትን ለመቀበል ትመጣላችሁን» (አሉ)፡፡
- 4. (ሙሐመድም) «ጌታዬ ቃልን ሁሉ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለ ሲኾን ያውቃል እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው» አለ፡፡
- 5. «በእውነቱ (ቁርኣኑ) የሕልሞች ቅዠቶች ነው፡፡ ይልቁንም ቀጠፈው እንዲያውም እርሱ ቅኔን ገጣሚ ነው፡፡ የቀድሞዎቹም እንደተላኩ (መልክተኛ ከኾነ) በተዓምር ይምጣብን» አሉ፡፡
- 6. ከእነሱ በፊት ያጠፋናት ከተማ አላመነችም፡፡ ታዲያ እነሱ ያምናሉን
- 7. ከአንተም በፊት ወደእነሱ የምናወርድላቸው የኾነን ሰዎችን እንጂ ሌላን አላክንም፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች ጠይቁ፡፡
- 8. ምግብን የማይበሉ አካልም አላደረግናቸውም፡፡ ዘውታሪዎችም አልነበሩም፡፡
- 9. ከዚያም ቀጠሮን ሞላንላቸው፡፡ አዳንናቸውም፡፡ የምንሻውንም ሰው (አዳን)፡፡ ወሰን አላፊዎቹንም አጠፋን፡፡
- 10. ክብራችሁ በውስጡ ያለበትን መጽሐፍ ወደእናንተ በእርግጥ አወረድን፡፡ አታውቁምን
- 11. በዳይም ከነበረች ከተማ ያጠፋናትና ከኋላዋም ሌሎችን ሕዝቦች ያስገኘነው ብዙ ናት፡፡
- 12. ቅጣታችንም በተሰማቸው ጊዜ እነርሱ ወዲያውኑ ከእርሷ (ለመሸሽ) ይገሠግሣሉ፡፡
- 13. አትገሥግሡ፤ ትለመኑም ይኾናልና፡፡ በእርሱ ወደ ተቀማጠላችሁበት ጸጋ ወደ መኖሪያዎቻችሁም ተመለሱ (ይባላሉ)፡፡
- 14. «ዋ ጥፋታችን! እኛ በእርግጥ በዳዮች ነበርን» ይላሉ፡፡
- 15. የታጨዱ ሬሳዎችም እስካደረግናቸው ድረስ ይህቺ ጠሪያቸው ከመኾን አልተወገደችም፡፡
- 16. ሰማይንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ ቀላጆች ኾነን አልፈጠርንም፡፡
- 17. መጫወቻን (ሚስትና ልጅን) ልንይዝ በሻን ኖሮ ከእኛ ዘንድ በያዝነው ነበር፡፡ (ግን) ሠሪዎች አይደለንም፡፡
- 18. በእርግጥ እውነትን በውሸት ላይ እንጥላለን፡፡ አንጎሉን ያፈርሰዋልም፡፡ ወዲያውም እርሱ ጠፊ ነው፡፡ ለእናንተም ከዚያ (ሚስትና ልጅ አለው በማለት) ከምትመጥኑት ነገር ብርቱ ቅጣት አላችሁ፤ (ወዮላችሁ)፡፡
- 19. በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የእርሱ ነው፡፡ እርሱ ዘንድ ያሉትም (መላእክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም፡፡ አይሰለቹምም፡፡
- 20. በሌሊትና በቀንም ያጠሩታል፤ አያርፉም፡፡
- 21. ይልቁንም ከምድር የኾኑን እነርሱ ሙታንን የሚያስነሱን አማልክት ያዙን (የለም)፡፡
- 22. በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፡፡ የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ፡፡
- 23. ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ (ፍጥረቶቹ) ግን ይጠየቃሉ፡፡
- 24. ይልቁንም ከእርሱ ሌላ አማልክትን ያዙን «አስረጃችሁን አምጡ፡፡ ይህ (ቁርኣን) እኔ ዘንድ ያለው ሕዝብ መገሰጫ ከእኔ በፊትም የነበሩት ሕዝቦች መገሰጫ ነው» በላቸው፡፡ በውነቱ አብዛኞቻቸው እውነቱን አያውቁም፡፡ ስለዚህ እነሱ እምቢተኞች ናቸው፡፡
- 25. ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡
- 26. «አልረሕማንም (ከመላእክት) ልጅን ያዘ» አሉ፡፡ ጥራት ተገባው፡፡ አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናቸው፡፡
- 27. በንግግር አይቀድሙትም፤ (ያላለውን አይሉም)፡፡ እነርሱም በትእዛዙ ይሠራሉ፡፡
- 28. በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም፡፡ እነርሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው፡፡
- 29. ከእነሱም «እኔ ከእርሱ ሌላ አምላክ ነኝ» የሚል ያንን ገሀነምን እንመነዳዋለን፡፡ እንደዚሁ በዳዮችን እንመነዳለን፡፡
- 30. እነዚያም የካዱት ሰማያትና ምድር የተጣበቁ የነበሩና የለያየናቸው መኾናችንን አያውቁምን ሕያው የኾነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን፡፡ አያምኑምን
- 31. በምድርም ውስጥ በእነሱ እንዳታረገርግ ጋራዎችን አደረግን፡፡ ይመሩም ዘንድ በእርሷ ውስጥ ሰፋፊ መንገዶችን አደረግን፡፡
- 32. ሰማይንም (ከመውደቅ) የተጠበቀ ጣራ አደረግን፡፡ እነርሱም ከተዓምራቶቿ ዘንጊዎች ናቸው፡፡
- 33. እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው፡፡ ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ፡፡
- 34. (ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊት ለማንም ሰው ዘለዓለም መኖርን አላደረግንም፡፡ ታዲያ ብትሞት እነሱ ዘውታሪዎች ናቸውን
- 35. ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፡፡ ለመፈተንም በክፉም በበጎም እንሞክራችኋለን፡፡ ወደኛም ትመለሳላችሁ፡፡
- 36. እነዚያም የካዱት ሰዎች ባዩህ ጊዜ መሳለቂያ አድርገው እንጂ አይይዙህም፡፡ እነሱ በአልረሕማን መወሳት እነርሱ ከሓዲዎች ሲሆኑ «ያ አማልክቶቻችሁን (በክፉ) የሚያነሳው ይህ ነውን» (ይላሉ)፡፡
- 37. ሰው ቸኳይ ሆኖ ተፈጠረ፡፡ ተዓምራቶቼን በእርግጥ አሳያችኋለሁና አታቻኩሉኝ፡፡
- 38. «ይህ ቀጠሮም መቼ ነው እውነተኞች ከኾናችሁ (አምጡት)» ይላሉ፡፡
- 39. እነዚያ የካዱት ከፊቶቻቸውና ከጀርባዎቻቸው ላይ እሳትን የማይከለክሉበትን እነሱም የማይረዳዱበትን ጊዜ ቢያውቁ ኖሮ (ይህንን አይሉም ነበር)፡፡
- 40. ይልቁንም (ሰዓቲቱ) በድንገት ትመጣቸዋለች፤ ታዋልላቸዋለችም፡፡ መመለሷንም አይችሉም፡፡ እነሱም አይቆዩም፡፡
- 41. ከአንተ በፊትም የነበሩት መልክተኞች በእርግጥ ተቀለደባቸው፡፡ በእነዚያም ከእነሱ ይቀልዱ በነበሩት በርሱ ይሳለቁበት የነበሩት (ቅጣት) ሰፈረባቸው፡፡
- 42. «ከአልረሕማን (ቅጣት) በሌሊትና በቀን የሚጠብቃችሁ ማነው» በላቸው፡፡ በእውነቱ እነሱ ከጌታቸው ግሳጼ (ከቁርአን) ዘንጊዎች ናቸው፡፡
- 43. ለእነሱ ከእኛ ሌላ የምትከላከልላቸው አማልክት አለቻቸውን ነፍሶቻቸውን መርዳትን አይችሉም፡፡ እነርሱም (ከሓዲዎቹ) ከእኛ አይጠበቁም፡፡
- 44. በእውነት እነዚህንና አባቶቻቸውን በእነሱ ላይ ዕድሜ እስከ ረዘመባቸው ድረስ አጣቀምናቸው፡፡ (ተታለሉም)፡፡ እኛ ምድርን ከጫፎችዋ የምናጎላት ኾነን ስንመጣባት አያዩምን እነሱ አሸናፊዎች ናቸውን
- 45. «የማስፈራራችሁ በተወረደልኝ ብቻ ነው፡፡ ግን ደንቆሮዎች በሚስፈራሩ ጊዜ ጥሪን አይሰሙም» በላቸው፡፡
- 46. ከጌታህ ቅጣትም ወላፈን ብትነካቸው «ዋ ጥፋታችን! እኛ በዳዮች ነበርን» ይላሉ፡፡
- 47. በትንሣኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን፡፡ ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም፡፡ (ሥራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን፡፡ ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ፡፡
- 48. ለሙሳና ለሃሩንም እውነትንና ውሸትን የሚለይን ብርሃንንም ለጥንቁቆችም መገሰጫን በእርግጥ ሰጠናቸው፡፡
- 49. ለእነዚያ ጌታቸውን በሩቅ ለሚፈሩት እነሱም ከሰዓቲቱ ተጨናቂዎች ለኾኑ (መገሰጫን ሰጠን)፡፡
- 50. ይህም (ቁርኣን) ያወረድነው የኾነ ብሩክ መገሰጫ ነው፡፡ ታዲያ እናንተ ለእርሱ ከሓዲዎች ናችሁን
- 51. ለኢብራሂምም ከዚያ በፊት ቅን መንገዱን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ እኛም በእርሱ (ተገቢነት) ዐዋቂዎች ነበርን፡፡
- 52. ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ይህቺ ቅርጻ ቅርጽ ያቺ እናንተ ለእርሷ ተገዢዎች የኾናችሁት ምንድን ናት» ባለ ጊዜ (መራነው)፡፡
- 53. «አባቶቻችንን ለእርሷ ተገዢዎች ኾነው አገኘን» አሉት፡፡
- 54. «እናንተም አባቶቻችሁም በእርግጥ በግልጽ ስህተት ውስጥ ነበራችሁ» አላቸው፡፡
- 55. «በምሩ መጣህልን ወይንስ አንተ ከሚቀልዱት ነህ» አሉት፡፡
- 56. «አይደለም ጌታችሁ የሰማያትና የምድር ጌታ ያ የፈጠራቸው ነው፡፡ እኔም በዚህ ላይ ከመስካሪዎቹ ነኝ» አለ፡፡
- 57. «በአላህም እምላለሁ ዟሪዎች ኾናችሁ ከሄዳችሁ በኋላ ጣዖቶቻችሁን ተንኮል እሠራባቸዋለሁ» (አለ)፡፡
- 58. (ዘወር ሲሉ) ስብርብሮችም አደረጋቸው፡፡ ለእነሱ የኾነ አንድ ታላቅ (ጣዖት) ብቻ ሲቀር ወደርሱ ይመለሱ ዘንድ (እርሱን ተወው)፡፡
- 59. «በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራ ማነው እርሱ በእርግጥ ከበደለኞች ነው» አሉ፡፡
- 60. «ኢብራሂም የሚባል ጎበዝ (በመጥፎ) ሲያነሳቸው ሰምተናል» ተባባሉ፡፡
- 61. «ይመሰክሩበት ዘንድ በሰዎቹ ዓይን (ፊት) ላይ አምጡት» አሉ፡፡
- 62. «ኢብራሂም ሆይ! በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራህ አንተ ነህን» አሉት፡፡
- 63. «አይደለም ይህ ታላቃቸው ሠራው፡፡ ይናገሩም እንደ ኾነ ጠይቋቸው» አለ፡፡
- 64. ወደ ነፍሶቻቸውም ተመለሱ፡፡ «እናንተ (በመጠየቃችሁ) በዳዮቹ እናንተው ናችሁም» ተባባሉ፡፡
- 65. ከዚያም በራሶቻቸው ላይ ተገለበጡ፡፡ «እነዚህ የሚናገሩ አለመኾናቸውን በእርግጥ ዐውቀሃል፤» (አሉ)፡፡
- 66. «ታዲያ ለእናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር ከአላህ ሌላ ትገዛላችሁን» አላቸው፡፡
- 67. «ፎህ! ለእናንተ ከአላህ ሌላ ለምትገዙትም ነገር፤ አታውቁምን» (አለ)፡፡
- 68. «ሠሪዎች እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት፡፡ አማልክቶቻችሁንም እርዱ» አሉ፡፡ (በእሳት ላይ ጣሉትም)፡፡
- 69. «እሳት ሆይ! በኢብራሂም ላይ ቀዝቃዛ፤ ሰላምም ሁኚ» አልን፡፡
- 70. በእርሱም ተንኮልን አሰቡ፡፡ በጣም ከሳሪዎችም አደረግናቸው፡፡
- 71. እርሱንና ሉጥንም ወደዚያች፤ በውስጧ ለዓለማት በረከትን ወደ አደረግንባት ምድር (በመውሰድ) አዳን፡፡
- 72. ለእርሱም ኢስሐቅን ያዕቆብንም ተጨማሪ አድርገን ሰጠነው፡፡ ሁሉንም መልካሞች አደረግን፡፤
- 73. በትዕዛዛችንም ወደ በጎ ሥራ የሚመሩ መሪዎች አደረግናቸው፡፡ ወደእነሱም መልካም ሥራዎችን መሥራትን፣ ሶላትንም መስገድን፣ ዘካንም መስጠትን አወረድን፡፡ ለእኛ ተገዢዎችም ነበሩ፡፡
- 74. ሉጥንም ፍርድንና ዕውቀትን ሰጠነው፡፡ ከዚያችም መጥፎ ሥራዎችን ትሠራ ከነበረችው ከተማ አዳንነው፡፡ እነሱ ክፉ ሰዎች አመጸኞች ነበሩና፡፡
- 75. በችሮታችንም ውስጥ አገባነው፡፡ እርሱ ከመልካሞቹ ነውና፡፡
- 76. ኑሕንም ከዚያ በፊት (ጌታውን) በጠራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ለእርሱም (ጥሪውን) ተቀበልነው፡፡ እርሱንም ቤተሰቦቹንም ከከባድ ጭንቅ አዳን፡፡
- 77. ከነዚያም በታምራቶቻችን ከአስተባበሉት ሕዝቦች (ተንኮል) ጠበቅነው፡፡ እነሱ ክፉ ሕዝቦች አመጸኞች ነበሩና፡፡ ሁሉንም አሰጠምናቸውም፡፡
- 78. ዳውድንና ሱለይማንንም በአዝመራው ነገር በሚፈርዱ ጊዜ የሕዝቦቹ ፍየሎች ሌሊት በርሱ ውስጥ በተሰማሩ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ፍርዳቸውንም ዐዋቂዎች ነበርን፡፡
- 79. ለሱለይማንም (ትክክለኛይቱን ፍርድ) አሳወቅናት፡፡ ለሁሉም ጥበብንና ዕውቀትን ሰጠን፡፡ ተራራዎችን ከዳውድ ጋር የሚያወድሱ ሲኾኑ ገራን፡፡ አእዋፍንም (እንደዚሁ ገራን)፡፡ ሠሪዎችም ነበርን፡፡
- 80. የብረት ልብስንም ሥራ ለእናንተ ከጦራችሁ ትጠብቃችሁ ዘንድ አስተማርነው፡፡ እናንተ አመስጋኞች ናችሁን
- 81. ለሱለይማንም ነፋስን በኀይል የምትነፍስ በትዕዛዙ ወደዚያች በእርሷ ውስጥ በረከትን ወደ አደረግንባት ምድር (ወደ ሻም) የምትፈስ ስትኾን (ገራንለት)፡፡ በነገሩ ሁሉም ዐዋቂዎች ነበርን፡፡
- 82. ከሰይጣናትም ለእርሱ (ሉልን ለማውጣት) የሚጠልሙንና ከዚያም ሌላ ያለን ሥራ የሚሠሩን (ገራንለት)፡፡ ለእነሱም ተጠባባቂዎች ነበርን፡፡
- 83. አዩብንም (ኢዮብን) ጌታውን «እኔ መከራ አገኘኝ አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ» ሲል በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
- 84. ለእርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ከጉዳትም በእርሱ ላይ የነበረውን ሁሉ አስወገድን፡፡ ቤተሰቦቹንም ከእነሱም ጋር መሰላቸውን ከእኛ ዘንድ ለችሮታና ለተገዢዎች ለማስገንዘብ ሰጠነው፡፡
- 85. ኢስማዒልንም ኢድሪስንም ዙልኪፍልንም (አስታውስ)፡፡ ሁሉም ከታጋሾቹ ናቸው፡፡
- 86. ከችሮታችንም ውስጥ አገባናቸው፡፡ እነሱ ከመልካሞቹ ናቸውና፡፡
- 87. የዓሳውንም ባለቤት ተቆጥቶ በኼደ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በእርሱም ላይ ፈጽሞ የማንፈርድበት መኾናችንን ጠረጠረ፡፡ (ዓሳም ዋጠው)፡፡ በጨለማዎችም ውስጥ ኾኖ ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ጥራት ይገባህ፡፡ እኔ በእርግጥ ከበዳዮቹ ነበርኩ በማለት ተጣራ፡፡
- 88. ለርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ከጭንቅም አዳነው፡፡ እንደዚሁም ምእመናንን እናድናለን፡፡
- 89. ዘከሪያንም «ጌታዬ ሆይ! ብቻዬን አትተወኝ፡፡ አንተም ከወራሾች ሁሉ በላጭ ነህ ሲል» ጌታውን በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
- 90. ለእርሱም ጥሪውን ተቀበልነው፡፡ ለእርሱም የሕያን ሰጠነው፡፡ ለእርሱም ሚስቱን አበጀንለት፡፡ እነርሱ በበጎ ሥራዎች የሚቻኮሉ ከጃዮችና ፈሪዎች ኾነው የሚለምኑንም ነበሩ፡፡ ለእኛ ተዋራጆችም ነበሩ፡፡
- 91. ያችንም ብልቷን የጠበቀቺውን በርሷም ውስጥ ከመንፈሳችን የነፋንባትን እርሷንም ልጅዋንም (እንደዚሁ) ለዓለማት ተዓምር ያደረግናትን (መርየምን አስታውስ)፡፡
- 92. ይህች (ሕግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ፡፡
- 93. በሃይማኖታቸውም ነገር በመካከላቸው ተለያዩ፡፡ ሁሉም ወደኛ ተመላሾች ናቸው፡፡
- 94. እርሱ ያመነ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች ማንኛውንም የሚሠራም ሰው፤ ምንዳውን አይነፈግም፡፡ እኛም ለእርሱ መዝጋቢዎች ነን፡፡
- 95. ባጠፋናትም ከተማ ላይ እነሱ (ወደኛ) የማይመለሱ መኾናቸው እብለት ነው፤ (ይመለሳሉ)፡፡
- 96. የእጁጅና መእጁጅም እነርሱ ከየተረተሩ የሚንደረደሩ ሲኾኑ (ግድባቸው) በተከፈተች ጊዜ፥
- 97. እውነተኛውም ቀጠሮ በቀረበ ጊዜ፥ ያን ጊዜ እነሆ የእነዚያ የካዱት ሰዎች ዓይኖች ይፈጥጣሉ፡፡ «ዋ ጥፋታችን! ከዚህ (ቀን) በእርግጥ በዝንጋቴ ላይ ነበርን፤ በእውነትም በዳዮች ነበርን» (ይላሉ)፡፡
- 98. እናንተ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውም (ጣዖታት) የገሀነም ማገዶዎች ናችሁ፡፡ እናንተ ለእርሷ ወራጆች ናችሁ፡፡
- 99. እነዚህ (ጣዖታት) አማልክት በነበሩ ኖሮ አይገቧዋትም ነበር፡፡ ግን ሁሉም በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
- 100. ለእነርሱ በእርሷ ውስጥ መንሰቅሰቅ አላቸው፡፡ እነርሱም በውስጧ (ምንንም) አይሰሙም፡፡
- 101. እነዚያ ከእኛ መልካሟ ቃል ለእነርሱ ያለፈችላቸው እነዚያ ከርሷ የተራቁ ናቸው፡፡
- 102. ድምጽዋን አይሰሙም፡፡ እነርሱም ነፍሶቻቸው በሚሹት ነገር ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
- 103. ታላቁ ድንጋጤ አያስተክዛቸውም፡፡ መላእክትም ይህ ያ ትቀጠሩ የነበራችሁት ቀናችሁ ነው፤ እያሉ ይቀበሏቸዋል፡፡
- 104. ለመጽሐፎች የኾኑ ገጾች እንደሚጠቀለሉ ሰማይን የምንጠቀልልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ የመጀመሪያን ፍጥረት እንደ ጀመርን እንመልሰዋለን፡፡ (መፈጸሙ) በእኛ ላይ የኾነን ቀጠሮ ቀጠርን፡፡ እኛ (የቀጠርነውን) ሠሪዎች ነን፡፡
- 105. ምድንም መልካሞቹ ባሮቼ ይወርሷታል ማለትን ከመጽሐፉ (ከተጠበቀው ሰሌዳ) በኋላ በመጽሐፎቹ በእርግጥ ጽፈናል፡፡
- 106. በዚህ (ቁርኣን) ውስጥ ለተገዢዎች ሕዝቦች በቂነት አልለ፡፡
- 107. (ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡
- 108. «ያ ወደኔ የሚወረደው አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን» በላቸው፡፡
- 109. እምቢም ቢሉ (በማወቅ) በእኩልነት ላይ ኾነን (የታዘዝኩትን) አስታውቅኋችሁ፡፡ «የምትስፈራሩበትም ነገር ቅርብ ወይም ሩቅ መኾኑን አላውቅም፤» በላቸው፡፡
- 110. እርሱ ከንግግር ጩኸትን ያውቃል፡፡ የምትደብቁትንም ሁሉ ያውቃል፡፡
- 111. እርሱም (ቅጣትን ማቆየት) ምናልባት ለእናንተ ፈተናና እስከ ጊዜው መጠቃቀሚያ እንደሆነም አላውቅም፤ (በላቸው)፡፡
- 112. «ጌታዬ ሆይ! በእውነት ፍረድ፤ ጌታችንም እጅግ በጣም ሩኅሩኅ በምትሉት ነገር ላይ መታገዣ ነው» አለ፡፡