2. ورَةُ البقرة - ቁርዓን
- 1. አ.ለ.መ
- 2. ይህ መጽሐፍ (ከአላህ ለመኾኑ) ጥርጥር የለበትም፤ ለፈራህያን መሪ ነው፡፡
- 3. ለነዚያ በሩቁ ነገር የሚያምኑ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው የሚሰግዱ ከሰጠናቸውም ሲሳይ የሚቸሩ ለኾኑት፤
- 4. ለእነዚያም ወደ አንተ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው የሚያምኑ በመጨረሻይቱም (ዓለም) እነርሱ የሚያረጋግጡ ለኾኑት (መሪ ነው)፡፡
- 5. እነዚያ ከጌታቸው በመመራት ላይ ናቸው፤ እነዚያም እነሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
- 6. እነዚያ የካዱት (ሰዎች) ብታስፈራራቸውም ባታስፈራራቸውም በነርሱ ላይ እኩል ነው፤ አያምኑም፡፡
- 7. አላህ በልቦቻቸው ላይ በመስሚያቸውም ላይ አትሞባቸዋል፤ በዓይኖቻቸውም ላይ መሸፈኛ አልለ፤ ለነሱም ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡
- 8. ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡
- 9. አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡