77. سورة المرسلات - ቁርዓን
- 1. ተከታታይ ኾነው በተላኩት፣
- 2. በኀይል መንፈስን ነፋሾች በኾኑትም፣
- 3. መበተንን በታኞች በኾኑትም፤ (ነፋሶች)፣
- 4. መለየትን ለይዎች በኾኑትም፣
- 5. መገሠጫን (ወደ ነቢያት) ጣይዎች በኾኑትም፣
- 6. ምክንያትን ለማስወገድ ወይም ለማስፈራራት (ጣይዎች በኾኑት መላእክት) እምላለሁ፡፡
- 7. ያ የምትስፈራሩበት (ትንሣኤ) በእርግጥ ኋኝ ነው፡፡
- 8. ከዋክብትም (ብርሃንዋ) በታበሰች ጊዜ፡፡
- 9. ሰማይም በተከፈተች ጊዜ፡፡
- 10. ጋራዎችም በተንኮተኮቱ ጊዜ፡፡
- 11. መልክተኞቹም ወቅት በተደረገላቸው ጊዜ፡፡
- 12. ለየትኛው ቀን ተቀጠሩ (የሚባል ሲኾን)፤
- 13. ለመለያው ቀን (በተባለ ጊዜ፤ በፍጡሮች መካከል ይፈረዳል)፡፡
- 14. የመለያውም ቀን ምን እንደኾነ ምን አሳወቀህ?
- 15. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 16. የፊተኞቹን (ሕዝቦች) አላጠፋንምን?
- 17. ከዚያም የኋለኞቹን እናስከትላቸዋለን፡፡
- 18. በአመጸኞች ሁሉ እንደዚሁ እንሠራለን፡፡
- 19. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 20. ከደካማ ውሃ አልፈጠርናችሁምን?
- 21. በተጠበቀ መርጊያ ውስጥም (በማሕፀን) አደረግነው፡፡
- 22. እስከ ታወቀ ልክ ድረስ፡፡ መጠንነውም፤ ምን ያማርንም
- 23. መጣኞች ነን!
- 24. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 25. ምድርን ሰብሳቢ አላደረግናትምን?
- 26. ሕያዋን ኾናችሁ ሙታንም ኾናችሁ፡፡
- 27. በውስጧም ከፍተኛዎችን ተራራዎች አደረግን፡፡ ጣፋጭ ውሃንም አጠጣናችሁ፡፡
- 28. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 29. «ወደዚያ በእርሱ ታስተባብሉ ወደ ነበራችሁት (ቅጣት) አዝግሙ፡፡
- 30. «ባለ ሦስት ቅርንጫፎች ወደ ኾነው ጥላ አዝግሙ፤» (ይባላሉ)፡፡
- 31. አጠላይ ያልኾነ ከእሳቱም ላንቃ የማያድን ወደ ኾነው (አዝግሙ)፡፡
- 32. እርሷ እንደ ታላላቅ ሕንጻ የኾኑን ቃንቄዎች ትወረውራለች፡፡
- 33. (ቃንቄውም) ልክ ዳለቻዎች ግመሎችን ይመስላል፡፡
- 34. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 35. ይህ የማይናገሩበት ቀን ነው፡፡
- 36. ይቅርታም ይጠይቁ ዘንድ፤ ለእነርሱ አይፈቀድላቸውም፡፡
- 37. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 38. ይህ መለያው ቀን ነው፡፡ እናንተንም የፊተኞቹንም ሰብሰብናችሁ፡፡
- 39. ለናንተም (ለማምለጥ) ብልሃት እንዳላችሁ ተተናኮሉኝ፡፡
- 40. ላስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 41. ጥንቁቆቹ በጥላዎችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡
- 42. ከሚከጅሉትም ሁሉ በፍራፍሬዎች ውስጥ ናቸው፡፡
- 43. «ትሠሩት በነበራችሁት ዋጋ የምትደሰቱ ኾናችሁ ብሉ፣ ጠጡም፤» (ይባላሉ)፡፡
- 44. እኛ እንደዚሁ መልካም ሠሪዎችን ሁሉ እንመነዳለን፡፡
- 45. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 46. ብሉ፤ ጥቂትንም (ጊዜ) ተጠቀሙ፡፡ እናንተ አመጸኞች ናችሁና፡፡
- 47. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 48. «ለእነርሱ ስገዱም» በተባሉ ጊዜ አይሰግዱም፡፡
- 49. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 50. ከእርሱም ሌላ በየትኛው ንግግር ያምናሉ?