91. سورة الشمس - ቁርዓን
- 1. በፀሐይና በብርሃኗ እምላለሁ፡፡
- 2. በጨረቃም በተከተላት ጊዜ፤
- 3. በቀኑም (ፀሐይን) በገለጻት ጊዜ፤
- 4. በሌሊቱም በሸፈናት ጊዜ፤
- 5. በሰማይቱም በገነባትም (ጌታ)፤
- 6. በምድሪቱም በዘረጋትም፤
- 7. በነፍስም ባስተካከላትም፤
- 8. አመጽዋንና ፍርሃትዋንም ባሳወቃት (አምላክ እምላለሁ)፡፡
- 9. (ከኀጢኣት) ያጠራት ሰው ፍላጎቱን በእርግጥ አገኘ፡፡
- 10. (በኀጢኣት) የሸፈናትም ሰው በእውነት አፈረ፡፡
- 11. ሠሙድ ወሰን በማለፍዋ አስተባበለች፡፡
- 12. ጠማማዋ በተንቀሳቀሰ ጊዜ፡፡
- 13. ለእነርሱም የአላህ መልክተኛ (ሷሊህ) «የአላህን ግመል የመጠጥ ተራዋንም (ተጠንቀቁ)» አላቸው፡፡
- 14. አስተባበሉትም፡፡ (ቋንጃዋን) ወጓትም፡፡ በኀጢኣታቸውም ምክንያት ጌታቸው (ቅጣትን) በእነርሱ ላይ ደመደመባቸው፤ አስተካከላትም፡፡
- 15. ፍጻሜዋንም (የምታስከትለውን) አያፈራም፡፡