71. سورة نوح - ቁርዓን
- 1. እኛ ኑሕን «ሕዝቦችህን አሳማሚ ቅጣት ሳይመጣባቸው በፊት አስጠንቅቅ በማለት ወደ ሕዝቦቹ ላክነው፡፡»
- 2. (እርሱም) አለ «ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ለእናንተ ገላጭ የኾንኩ አስጠንቃቂ ነኝ፡፡
- 3. «አላህን ተገዙት፣ ፍሩትም፣ ታዘዙኝም በማለት፤ (አስጠንቃቂ ነኝ)፡፡
- 4. «ለእናንተ ከኀጢኣቶቻችሁ ይምራልና፡፡ ወደተወሰነው ጊዜም ያቆያችኋል፡፡ የአላህ (የወሰነው) ጊዜ በመጣ ወቅት አይቆይም፡፡ የምታውቁት ብትኾኑ ኖሮ (በታዘዛችሁ ነበር)፡፡»
- 5. (ስለ ተቃወሙትም) «አለ ጌታዬ ሆይ! እኔ ሌሊትም ቀንም ሕዝቦቼን ጠራሁ፡፡
- 6. «ጥሪየም መሸሽን እንጅ ሌላ አልጨመረላቸውም፡፡
- 7. «እኔም ለእነርሱ ትምር ዘንድ (ወደ እምነት) በጠራኋቸው ቁጥር ጣቶቻቸውን በጆሮዎቻቸው ውስጥ አደረጉ፡፡ ልብሶቻቸውንም ተከናነቡ፡፡ (በመጥፎ ሥራቸው ላይ) ዘወተሩም፡፡ (ያለ ልክ) መኩራትንም ኮሩ፡፡
- 8. «ከዚያም እኔ በጩኸት ጠራኋቸው፡፡
- 9. «ከዚያም እኔ ለእነርሱ ገለጽኩ፡፡ ለእነርሱም መመስጠርን መሰጠርኩ
- 10. «አልኳቸውም፡- ጌታችሁን ምሕረትን ለምኑት፡፡ እርሱ በጣም መሐሪ ነውና፡፡
- 11. «በእናንተ ላይ ዝናምን ተከታታይ አድርጎ ይልካል፡፡
- 12. «በገንዘቦችና በልጆችም ይለግሰላችኋል፡፡ ለእናንተም አትክልቶችን ያደርግላችኋል፡፡ ለእናንተም ወንዞችን ያደርግላችኋል፡፡»
- 13. ለአላህ ልቅናን የማትሹት ለእናንተ ምን አላችሁ?
- 14. በልዩ ልዩ ኹኔታዎች በእርግጥ የፈጠራችሁ ሲኾን፡፡
- 15. አላህ ሰባትን ሰማያት አንዱ ካንዱ በላይ ሲኾን እንዴት እንደፈጠረ አታዩምን?
- 16. በውስጣቸውም ጨረቃን አብሪ አደረገ፡፡ ፀሐይንም ብርሃን አደረገ፡፡
- 17. አላህም ከምድር ማብቀልን አበቀላችሁ፡፡
- 18. ከዚያም በውስጧ ይመልሳችኋል፡፡ ማውጣትንም ያወጣችኋል፡፡
- 19. አላህም ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ አደረጋት፡፡
- 20. ከእርሷ ሰፋፊዎችን መንገዶች ትገቡ ዘንድ፡፡
- 21. ኑሕ አለ፡- «ጌታዬ ሆይ! እነሱ አምመጹብኝ፡፡ ገንዘቡና ልጁም ከጥፋት በስተቀር ያልጨመረለትን ሰው ተከተሉ፡፡
- 22. «ታላቅንም ተንኮል የመከሩትን ሰዎች» (ተከተሉ)፡፡
- 23. አሉም «አምላኮቻችሁን አትተዉ፡፡ ወድንም፣ ሱዋዕንም፣ የጉሥንም፣ የዑቅንም ነስርንም አትተው፡፡
- 24. «በእርግጥም ብዙዎችን አሳሳቱ፡፡ ከሓዲዎችንም ጥመትን እንጅ ሌላን አትጨምርላቸው» (አለ)፡፡
- 25. በኀጢኣቶቻቸው ምክንያት ተሰጠሙ፡፡ እሳትንም እንዲገቡ ተደረጉ፡፡ ለእነርሱም ከአላህ ሌላ የኾኑ ረዳቶችን አላገኙም፡፡
- 26. ኑሕም አለ «ጌታዬ ሆይ! ከከሓዲዎቹ በምድር ላይ አንድንም አትተው፡፡
- 27. «አንተ ብትተዋቸው ባሮችህን ያሳስታሉና፡፡ ኀጢኣተኛ ከሓዲንም እንጅ ሌላን አይወልዱም፡፡
- 28. «ጌታዬ ሆይ! ለእኔም ለወላጆቼም ምእመን ኾኖ በቤቴ ለገባም ሰው ሁሉ ለምእመናንና ለምእምናትም ምሕረት አድርግ፡፡ ከሓዲዎችንም ከጥፋት በቀር አትጨምርላቸው፤» (አለ)፡፡