36. سورةيس - ቁርዓን
- 1. የ.ሰ.(ያ ሲን)
- 2. ጥበብ በተመላበት ቁርኣን እምላለሁ፡፡
- 3. አንተ በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ፡፡
- 4. በቀጥታም መንገድ ላይ ነህ፡፡
- 5. አሸናፊ አዛኝ ከሆነው አምላክ መወረድን ተወረደ፡፡
- 6. አባቶቻቸው ያልተስፈራሩትን ሕዝቦች ልታስጠነቅቅበት (ተወረደ)፡፡ እነርሱ ዘንጊዎች ናቸውና፡፡
- 7. በአብዛኞቻቸው ላይ ቃሉ በእውነት ተረጋገጠ፡፡ ስለዚህ እነርሱ አያምኑም፡፡
- 8. እኛ በአንገቶቻቸው ላይ እንዛዝላዎችን አደረግን፡፡ እርሷም (እንዛዝላይቱ) ወደ አገጮቻቸው ደራሽ ናት፡፡ እነርሱም ራሶቻቸውን ያንጋጠጡ ናቸው፡፡
- 9. ከስተፊታቸውም ግርዶን ከስተኋላቸውም ግርዶን አደረግን፡፡ ሸፈንናቸውም፡፡ ስለዚህ እነሱ አያዩም፡፡
- 10. ብታሰጠነቅቃቸውም ባታስጠነቅቃቸውም በእነርሱ ላይ እኩል ነው፡፡ አያምኑም፡፡
- 11. የምታስጠነቅቀው ግሳጼን የተከተለንና አልረሕማንን በሩቅ የፈራን ሰው ብቻ ነው፡፡ በምሕረትና በመልካም ምንዳም አብስረው፡፡
- 12. እኛ ሙታንን እኛ በእርግጥ ሕያው እናደርጋለን፡፡ ያስቀደሙትንም ሥራ ፈለጎቻቸውንም እንጽፋለን፡፡ ነገሩንም ሁሉ ገላጭ መሪ በኾነ መጽሐፍ ውስጥ አጠቃለልነው፡፡
- 13. ለእነርሱም የከተማይቱን (የአንጾኪያን) ሰዎች ምሳሌ መልክተኞቹ በመጧት ጊዜ (የኾነውን) ግለጽላቸው፡፡
- 14. ወደእነርሱ ሁለትን ሰዎች በላክንና ባስተባበሉዋቸው ጊዜ በሶስተኛም በአበረታንና እኛ ወደ እናንተ መልክተኞች ነን ባሏቸው ጊዜ (የኾነውን ምሳሌ ግለጽላቸው)፡፡
- 15. እናንተ መሰላችን ሰዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም፡፡ አልረሕማንም ምንም ነገር አላወረደም፡፡ እናንተ የምትዋሹ እንጂ ሌላ አይደላችሁም አሉዋቸው፡፡
- 16. (መልክተኞቹም) አሉ «ጌታችን ያውቃል፡፡ እኛ ወደእናንተ በእርግጥ መልክተኞች ነን፡፡
- 17. «በእኛ ላይም ግልጽ የኾነ ማድረስ እንጂ ሌላ የለብንም፡፡»
- 18. (ሕዝቦቹም) «እኛ በእናንተ ገደ ቢሶች ኾን፡፡ ባትከለከሉ በእርግጥ እንወግራችኋለን፡፡ ከእኛም አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ያገኛችኋል» አሉ፡፡
- 19. «ገደ ቢስነታችሁ ከእናንተው ጋር ነው፡፡ ብትገሰጹ (ትዝታላችሁን?) በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ» አሏቸው፡፡
- 20. ከከተማይቱም ሩቅ ዳርቻ የሚሮጥ ሰው መጣ፡፡ «ወገኖቼ ሆይ! መልክተኞቹን ተከተሉ» አለ፡፡
- 21. «እነርሱ ቅኑን መንገድ የተመሩ ሲኾኑ ዋጋን የማየጠይቁዋችሁን ሰዎች ተከተሉ» (አላቸው)፡፡
- 22. «ያንንም የፈጠረኝን፤ ወደርሱም የምትመለሱበትን (ጌታ) የማልገዛ ለእኔ ምን አለኝ?» (አለ)፡፡
- 23. «ከእርሱ ሌላ አማልክትን እይዛለሁን? አልረህማን በጉዳት ቢሻኝ ምልጃቸው ከእኔ (ለመመለስ) ምንም አትጠቅመኝም፤ አያድኑኝምም፡፡
- 24. «እኔ ያን ጊዜ በግልጽ ስህተት ውስጥ ነኝ፡፡
- 25. «እኔ በጌታችሁ አመንኩ፤ ስሙኝም፤» (አለ)፡፡
- 26. «ገነትን ግባ» ተባለ፡፡ (እርሱም) አለ፡- «ወገኖቼ ቢያውቁ እመኛለሁ፡፡
- 27. «ጌታዬ ለእኔ ምሕረት ያደረገልኝና ከተከበሩትም ያደረገኝ መኾኑን፡፡»
- 28. ከእርሱም በኋላ በሕዝቦቹ ላይ (ልናጠፋቸው) ሰራዊትን ከሰማይ አላወረድንም፡፡ (በማንም ላይ) አወራጆችም አልነበርንም፡፡
- 29. (ቅጣታቸው) አንዲት ጩኸት እንጂ ሌላ አልነበረችም፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ ጠፊዎች ኾኑ፡፡
- 30. በባሮቹ ላይ ዋ ቁልጭት! ከመልክተኛ አንድም አይመጣቸውም በእርሱ የሚሳለቁበት ቢኾኑ እንጅ፡፡
- 31. ከእነርሱ በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን ማጥፋታችንንና እነርሱ ወደነርሱ የማይመለሱ መኾናቸውን አላወቁምን?
- 32. ሁሉም እኛ ዘንድ የሚሰበሰቡ የሚቀረቡ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡
- 33. የሞተችውም ምድር ለእነርሱ ምልክት ናት! ሕያው አደረግናት፡፡ ከእርሷም ፍሬን አወጣን፤ ከርሱም ይበላሉ፡፡
- 34. በእርሷም ውሰጥ ከዘምበባዎችና ከወይኖች የኾኑ አትክልቶችን አደረግን፡፡ በእርሷም ውስጥ ምንጮችን አፈለቅን፡፡
- 35. ከፍሬውና እጆቻቸው ከሠሩትም ይበሉ ዘንድ (ይህን አደረግን)፤ አያመሰግኑምን?
- 36. ያ ምድር ከምታበቅለው ከነፍሶቻቸውም ከማያውቁትም ነገር ዓይነቶችን ሁሏንም የፈጠረ (አምላክ) ጥራት ይገባው፡፡
- 37. ሌሊቱም ለእነርሱ ምልክት ነው፡፡ ከእርሱ ላይ ቀንን እንገፍፋለን፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ በጨለማ ውስጥ ይገባሉ፡፡
- 38. ፀሐይም ለእርሷ ወደ ሆነው መርጊያ ትሮጣለች፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው፡፡
- 39. ጨረቃንም የመስፈሪያዎች ባለቤት ሲኾን እንደ ዘንባባ አሮጌ ቀንዘል እስኪኾን ድረስ (መኼዱን) ለካነው፡፡
- 40. ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም፡፡ ሌሊትም ቀንን (ያለ ጊዜው) ቀዳሚ አይኾንም፡፡ ሁሉም በመዞሪያቸው ውስጥ ይዋኛሉ፡፡
- 41. እኛም (የቀድሞ) ትውልዳቸውን በተሞላች መርከብ ውስጥ የጫን መኾናችን ለእነርሱ ምልክት ነው፡፡
- 42. ከመሰሉም በእርሱ የሚሳፈሩበትን ለእነርሱ ፈጠርንላቸው፡፡
- 43. ብንሻም እናሰጥማቸዋለን፡፡ ለእነርሱም ረዳት የላቸውም፡፡ እነርሱም የሚድዳኑ አይደሉም፡፡
- 44. ግን ከእኛ ለኾነው ችሮታና እስከ ጊዜ ሞታቸው ለማጣቀም (አዳንናቸው)፡፡
- 45. ለእነርሱም «በስተፊታችሁና በኋለችሁ ያለውን ነገር ተጠንቀቁ ይታዘንላችኋልና» በተባሉ ጊዜ (ፊታቸውን ያዞራሉ)፡፡
- 46. ከጌታቸውም ተዓምራት ማንኛይቱም ተዓምር አትመጣላቸውም፤ ከእርሷ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጅ፡፡
- 47. ለእነርሱም «አላህ ከሰጣችሁ ሲሳይ ለግሱ» በተባሉ ጊዜ እነዚያ የካዱት ለእነዚያ ላመኑት «አላህ ቢሻ ኖሮ የሚያበላውን ሰው እናበላለን? እናንተ በግልጽ ስህተት ውስጥ እንጂ በሌላ ላይ አይደላችሁም» ይላሉ፡፡
- 48. «እውነተኞችም እንደኾናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡
- 49. እነርሱ የሚከራከሩ ሲኾኑ በድንገት የምትይዛቸው የኾነችን አንዲትን ጩኸት እንጂ ሌላን አይጠባበቁም፡፡
- 50. (ያን ጊዜ) መናዘዝንም አይችሉም፡፡ ወደ ቤተሰቦቻቸወም አይመለሱም፡፡
- 51. በቀንዱም ይነፋል፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ ከመቃብሮቻቸው ወደ ጌታቸው በፍጥነት ይገሰግሳሉ፡፡
- 52. «ወይ ጥፋታችን! ከመኝታችን ማን ቀሰቀሰን? ይህ ያ አዛኙ ጌታ (በእርሱ) የቀጠረን መልክተኞቹም እውነትን የነገሩን ነው» ይላሉ፡፡
- 53. (እርሷ) አንዲት ጩኸት እንጂ አይደለችም፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ እኛ ዘንድ የሚሰበሰቡ የሚቀርቡ ናቸው፡፡
- 54. «ዛሬም ማንኛይቱም ነፍስ ምንም አትበደልም፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን እንጂ ሌላን አትመነዱም» (ይባላሉ)፡፡
- 55. የገነት ሰዎች ዛሬ በእርግጥ በሥራዎች ውስጥ ተደሳቾች ናቸው፡፡
- 56. እነርሱም ሚስቶቻቸውም በጥላዎች ውስጥ ናቸው፡፡ ባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ናቸው፡፡
- 57. በውስጧ ለእነርሱ ፍራፍሬዎች አሏቸው፡፡ ለእነርሱም የሚፈልጉት ሁሉ አልላቸው፡፡
- 58. (ለእነርሱም) አዛኝ ከሆነው ጌታ በቃል ሰላምታ አላቸው።
- 59. (ይላልም) «እናንተ አመጸኞች ሆይ! ዛሬ (ከምእምናን) ተለዩ፡፡»
- 60. የአደም ልጆች ሆይ! ሰይጣንን አትገዙ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና በማለት ወደእናንተ አላዘዝኩምን?
- 61. ተገዙኝም፤ ይህ ቀጥተኘ መንገድ ነው፤ (በማለትም)፡፡
- 62. ከእናንተም ብዙን ፍጡር በእርግጥ አሳስቷል፡፡ የምታውቁም አልነበራችሁምን?
- 63. ይህቺ ያቺ ትቀጠሩዋት የነበረችው ገሀነም ናት፡፡
- 64. ትክዱ በነበራችሁት ምክንያት ዛሬ ግቧት (ይባላሉ)፡፡
- 65. ዛሬ በአፎቻቸው ላይ እናትምና እጆቻቸው ያነጋግሩናል፡፡ እግሮቻቸውም ይሠሩት በነበሩት ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡
- 66. ብንሻም ኖሮ በዐይኖቻቸው ላይ በአበስን ነበር፡፡ መንገድንም (እንደ ልመዳቸው) በተሽቀዳደሙ ነበር፡፡ እንዴትም ያያሉ?
- 67. ብንሻም ኖሮ በስፍራቸው ላይ እንዳሉ ወደ ሌላ ፍጥረት በለወጠናቸው ነበር፡፡ መኼድንም መመለስንም ባልቻሉም ነበር፡፡
- 68. ዕድሜውንም የምናረዝመውን ሰው በፍጥረቱ (ወደ ደካማነት) እንመልሰዋለን፤ አያውቁምን?
- 69. (ሙሐመድን) ቅኔንም አላስተማርነውም፡፡ ለእርሱም አይግገባውም፡፡ እርሱ (መጽሐፉ) መገሰጫና ገላጭ ቁርኣን እንጅ (ቅኔ) አይደለም፡፡
- 70. (ግሣጼነቱም ልቡ) ሕያው የኾነን ሰው ሊያስፈራራበትና ቃሉም በከሓዲዎች ላይ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡
- 71. እኛ እጆቻችን (ኃይሎቻችን) ከሠሩት ለእነርሱ እንስሳዎችን መፍጠራችንን አያውቁምን? እነርሱም ለእርሷ ባለ መብቶች ናቸው፡፡
- 72. ለእነርሱም ገራናት፡፡ ስለዚህ ከእርሷ ውስጥ የሚጋልቡት አልለ፡፡ ከእርሷም ይበላሉ፡፡
- 73. ለእነርሱም በእርሷ ውስጥ (ሌሎች) ጥቅሞች መጠጦችም አሉዋቸው፡፡ ታዲያ አያመሰግኑምን;
- 74. መረዳትንም በመከጀል ከአላህ ሌላ አማልክትን ያዙ፡፡
- 75. መርዳታቸውን አይችሉም፡፡ እነርሱም ለእርሳቸው (ወደ እሳት) የተቀረቡ ሰራዊት ናቸው፡፡
- 76. ንግግራቸውም አያሳዝንህ፡፡ እኛ የሚደብቁትንም የሚገልጹትንም እናውቃለንና፡፡
- 77. ሰውየው እኛ ከፍቶት ጠብታ የፈጠርነው መኾናችን አላወቀምን? ወዲያውም እርሱ (ትንሣኤን በመካድ) ግልጽ ተከራካሪ ይኾናልን?
- 78. ለእኛም ምሳሌን አደረገልን፡፡ መፈጠሩንም ረሳ፡፡ «አጥንቶችን እነርሱ የበሰበሱ ሲኾኑ ሕያው የሚያደርጋቸው ማነው?» አለ፡፡
- 79. «ያ በመጀመሪያ ጊዜ (ከኢምንት) ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል፡፡ እርሱም በፍጡሩ ሁሉ (ኹኔታ) ዐዋቂ ነው» በለው፡፡
- 80. ያ ለእናንተ በእርጥብ ዛፍ እሳትን ያደረገላችሁ ነው፡፡ ወዲያውኑም እናንተ ከእርሱ ታቀጣጥላላችሁ፡፡
- 81. ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ አይደለምን? ነው እንጅ፡፡ እርሱም በብዙ ፈጣሪው ዐዋቂው ነው፡፡
- 82. ነገሩም አንዳችን በሻ ጊዜ ኹን ማለት ነው፡፡ ወዲያው ይኾናልም፡፡
- 83. ያ የነገሩ ሁሉ ስልጣን በእጁ የኾነው ጌታ ጥራት ይገባው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡