68. سورة القلم - ቁርዓን
- 1. ነ.(ኑን)፤ በብርእ እምላለሁ በዚያም (መልአኮች) በሚጽፉት፡፡
- 2. አንተ በጌታህ ጸጋ የተጎናጸፍክ ስትኾን ዕብድ አይደለህም፡፡
- 3. ላንተም (ከጌታህ) የማይቋረጥ ዋጋ በእርግጥ አልለህ፡፡
- 4. አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡
- 5. ወደፊትም ታያለህ፤ ያያሉም፡፡
- 6. ዕብደት በማንኛችሁ እንዳልለ፡፡
- 7. ጌታህ እርሱ ከመንገዱ የተሳሳተውን ሰው ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱም ተመሪዎቹን ዐዋቂ ነው፡፡
- 8. ለአስተባባዮችም አትታዝዙ፡፡
- 9. ብትመሳሰላቸውና ቢመሳሰሉህ ተመኙ፡፡
- 10. ወራዳንም ሁሉ አትታዘዝ፡፡
- 11. ሰውን አነዋሪንና በማሳበቅ ኼያጅን፡፡
- 12. ለበጎ ነገር በጣም ከልካይን፣ ወሰን አላፊን፣ ኃጢአተኛን፤
- 13. ልበ ደረቅን፣ ከዚህ በኋላ ዲቃላን (ሁሉ አትታዘዝ)፡፡
- 14. የገንዘብና የልጆች ባለቤት በመኾኑ (ያስተባብላል)፡፡
- 15. በእርሱ ላይ አንቀጾቻችን በሚነበቡ ጊዜ «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናቸው» ይላል፡፡
- 16. በአፍንጫው ላይ በእርግጥ (የሚነወርበት) ምልክት እናደርግበታለን፡፡
- 17. እኛ የአትክልቲቱን ባለቤቶቸ እንደ ሞከርን (የመካን ሰዎች) ሞከርናቸው፡፡ ማልደው (ፍሬዋን) ሊለቅሟት በማሉ ጊዜ፡፡
- 18. (በመሓላቸው) አያስቀሩምም፡፡
- 19. እነርሱ የተኙ ኾነውም ሳሉ ከጌታህ የኾነ ዟሪ በእርሷ ላይ ዞረባት፡፡
- 20. እንደ ሌሊት ጨለማም ኾና አነጋች፤ (ከሰለች)፡፡
- 21. ያነጉም ኾነው ተጠራሩ፡፡
- 22. «ቆራጮች እንደ ኾናችሁ በእርሻቸሁ ላይ ማልዱ» በማለት፡፡
- 23. እነርሱ የሚንሾካሾኩ ኾነው ኼዱም፡፡
- 24. ዛሬ በእናንተ ላይ ድኻ እንዳይገባት በማለት፡፡
- 25. (ድኾችን) በመከልከልም ላይ (በሐሳባቸው) ቻዮች ኾነው ማለዱ፡፡
- 26. (ተቃጥላ) ባዩዋትም ጊዜ «እኛ በእርግጥ ተሳሳቾች ነን» አሉ፡፡
- 27. «ይልቁንም እኛ የተከለከልን ነን» አሉ፡፡
- 28. ትክክለኛቸው «ለእናንተ አላህን ለምን አታጠሩም አላልኳችሁምን?» አላቸው፡፡
- 29. «ጌታችን ጥራት ይገባው፡፡ እኛ በዳዮች ነበርን፤» አሉ፡፡
- 30. የሚወቃቀሱም ኾነው ከፊሎቻቸው በከፊሉ ላይ መጡ፡፡
- 31. «ዋ ጥፋታችን! እኛ ድንበር አላፊዎች ነበርን፤» አሉ፡፡
- 32. «ጌታችን ከእርሷ የተሻለን (አትክልት) ሊለውጠን ይከጀላል፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ከጃዮች ነን፤» (አሉ)፡፡
- 33. ቅጣቱ እንደዚሁ ነው፡፡ የመጨረሻይቱም ዓለም ቅጣት ታላቅ ነው፡፡ የሚያውቁት በኾኑ ኖሮ (በተጠነቀቁ ነበር)፡፡
- 34. ለጥንቁቆቹ በጌታቸው ዘንድ መጠቀሚያ ገነቶች አሏቸው፡፡
- 35. ሙስሊሞቹን እንደ ከሓዲዎች እናደርጋለን?
- 36. ለእናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ፡፡
- 37. በእውነቱ ለእናንተ በእርሱ የምታጠኑበት መጽሐፍ አላችሁን?
- 38. በውስጡ ለእናንተ የምትመርጡት አላችሁ (የሚል)
- 39. ወይስ ለእናንተ የምትፈርዱት አላችሁ በማለት (ቃል ኪዳን የገባንላችሁ) እስከ ትንሣኤ ቀን ደራሽ የኾኑ መሓላዎች ለእናንተ በእኛ ላይ አሏችሁን?
- 40. በዚህ ማንኛቸው ተያያዥ እንደ ኾነ ጠይቃቸው፡፡
- 41. ወይስ ለእነርሱ (በፍርዳቸው ተስማሚ) «ተጋሪዎች» አሏቸውን? እውነተኞችም እንደኾኑ «ተጋሪዎቻቸውን» ያምጡ፡፡
- 42. ባት የሚገለጥበትን (ከሓዲዎች) ወደ መስገድም የሚጥጠሩበትንና የማይችሉበት ቀን (አስታውስ)፡፡
- 43. ዓይኖቻቸው የፈሩ ውርደት የምትሸፍናቸው ሲኾኑ፤ (ወደ ስግደት የሚጠሩበትን)፤ እነርሱም (በምድረ ዓለም) ደህና ኾነው ሳሉ ወደ ስግደት በእርግጥ ይጠሩ ነበሩ፡፡
- 44. በዚህም ንግግር ከሚያስተባብሉት ሰዎች ጋር ተዎኝ፡፡ (እነርሱን እኔ እበቃሃለሁ)፡፡ ከማያውቁት ስፍራ አዘናግተን እንይዛቸዋለን፡፡
- 45. እነርሱንም አዘገያለሁ፡፡ ዘዴዬ ብርቱ ነውና፡፡
- 46. በእውነቱ ዋጋን ትጠይቃቸዋለህን? ስለዚህ እነርሱ ከዕዳ የተከበዱ ናቸውን?
- 47. ወይስ እነርሱ ዘንድ የሩቁ ምስጢር ዕውቀት አልለን? ስለዚህ እነርሱ ይጽፋሉን?
- 48. ለጌታህም ፍርድ ታገሥ፤ (በመበሳጨትና ባለ መታገሥ) እንደ ዓሣው ባለቤትም (እንደ ዮናስ) አትኹን፡፡ እርሱ በጭንቀት የተመላ ኾኖ (ጌታውን) በተጣራ ጊዜ፡፡
- 49. ከጌታው የኾነ ጸጋ ባላገኘው ኖሮ በምድረ በዳ ተወቃሽ ኾኖ በተጣለ ነበር፡፡
- 50. ጌታውም (በነቢይነት) መረጠው፡፡ ከደጋጎቹም አደረገው፡፡
- 51. እነሆ እነዚያም የካዱት ሰዎች ቁርኣኑን በሰሙ ጊዜ በዓይኖቻቸው ሊጥሉህ (ሊያጠፉህ) ይቀርባሉ፡፡ «እርሱም በእርግጥ ዕብድ ነው» ይላሉ፡፡
- 52. ግን እርሱ (ቁርኣን) ለዓለማት መገሰጫ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡