12. سورة يوسف - ቁርዓን
- 1. አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ) እነዚህ የገላጩ መጽሐፍ አንቀጾች ናቸው፡፡
- 2. እኛ (ፍቹን) ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን ሲሆን በእርግጥ አወረድነው፡፡
- 3. እኛ ይህንን ቁርኣን ወደ አንተ በማውረዳችን በጣም መልካም ዜናዎችን በአንተ ላይ እንተርክልሃለን፡፡ እነሆ ከእርሱ በፊት (ካለፉት ሕዝቦች ታሪክ) በእርግጥ ከዘንጊዎቹ ነበርክ፡፡
- 4. ዩሱፍ ለአባቱ፡- «አባቴ ሆይ! እኔ ዐስራ አንድ ከዋክብትን ፀሐይንና ጨረቃንም (በሕልሜ) አየሁ፡፡ ለእኔ ሰጋጆች ሆነው አየኋቸው» ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
- 5. (አባቱም) አለ «ልጄ ሆይ! ሕልምህን ለወንድሞችህ አታውራ፡፡ ላንተ ተንኮልን ይሰሩብሃልና፡፡ ሰይጣን ለሰው ግልጽ ጠላት ነውና፡፡»
- 6. «እንደዚሁም (እንዳየኸው) ጌታህ ይመርጥሃል፡፡ ከንግግሮችም ፍች ያስተምርሃል፡፡ ጸጋውንም ከአሁን በፊት በሁለቱ አባቶችህ በኢብራሂምና በኢስሐቅ ላይ እንዳሟላት በአንተ ላይና በያዕቆብ ዘሮችም ላይ ይሞላታል፡፡ ጌታህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡»
- 7. በዩሱፍና በወንድሞቹ (ታሪኮች) ውስጥ ለጠያቂዎች ሁሉ በእርግጥ አስደናቂ ምልክቶች ነበሩ፡፡
- 8. (ወንድሞቹ) ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «እኛ ጭፍሮች ስንሆን ዩሱፍና ወንድሙ (ብንያም) ወደ አባታችን ከእኛ ይበልጥ የተወደዱ ናቸው፡፡ አባታችን በግልጽ ስህተት ውስጥ ነው፡፡