78. سورة النبإ - ቁርዓን
- 1. ከምን ነገር ይጠያየቃሉ?
- 2. ከታላቁ ዜና (ከቁርኣን ይጠያየቃሉ)፡፡
- 3. ከዚያ እነርሱ በእርሱ የተለያዩበት ከኾነው፡፡
- 4. ይከልከሉ፤ ወደፊት (የሚደርስበቸውን) በእርግጥ ያውቃሉ፡፡
- 5. ከዚያም ይከልከሉ፤ ወደፊት ያውቃሉ፡፡
- 6. ምድርን ምንጣፍ አላደረግንምን?
- 7. ጋራዎችንም ችካሎች አላደረግንምን?
- 8. ብዙ ዓይነቶችም አድርገን ፈጠርናችሁ፡፡
- 9. እንቅልፋችሁንም ዕረፍት አደረግን፡፡
- 10. ሌሊቱንም ልባስ አደረግን፡፡
- 11. ቀኑንም (ለኑሮ) መስሪያ አደረግን፡፡
- 12. ከበላያችሁም ሰባትን ብርቱዎች (ሰማያት) ገነባን፡፡
- 13. አንጸባራቂ ብርሃንንም አደረግን፡፡
- 14. ከአረገዙት ደመናዎችም ተንቧቢ ውሃን አወረድን፡፡
- 15. በእርሱ እኽልንና ቅጠላ ቅጠልን እናወጣ ዘንድ (አወረድን)፡፡
- 16. የተቆላለፉ አትክልቶችንም፡፡
- 17. የመለያው ቀን የተወሰነ ጊዜ ነው፡፡
- 18. በቀንዱ በሚነፋና የተለያዩ ጭፍሮች ኾናችሁ በምትመጡ ቀን ነው፡፡
- 19. ሰማይም በምትከፈትና (ባለ) ደጃፎችም በምትኾንበት፡፡
- 20. ጋራዎችም በሚነዱበት (እንደ) ሲሪብዱም በሚኾኑበት (ቀን) ነው፡፡
- 21. ገሀነም መጠባበቂያ (ስፍራ) ናት፡፡
- 22. ለሕግ ተላላፊዎች መመለሻ ስትኾን፡፡
- 23. በውስጧ ብዙን ዘመናት ነዋሪዎች ሲኾኑ፤
- 24. በውስጧ ቅዝቃዜንም መጠጥንም አይቀምሱም፡፡
- 25. ግን ሙቅ ውሃንና እዥን (ይቀምሳሉ)፡፡
- 26. ተስማሚን ምንዳ ይምመነዳሉ፡፡
- 27. እነርሱ ምርመራን የማይፈሩ ነበሩና፡፡
- 28. በአንቀጾቻችንም ማስተባበልን አስተባበሉና፡፡
- 29. ነገሩንም ሁሉ የተጻፈ ሲኾን አጠቃለልነው፡፡
- 30. ቅመሱም ቅጣትንም እንጅ (ሌላን) አንጨምራችሁም (ይባላሉ)፡፡
- 31. ለጥንቁቆቹ መዳኛ ስፍራ አልላቸው፡፡
- 32. አትክልቶችና ወይኖችም፡፡
- 33. እኩያዎች የኾኑ ጡተ ጉቻማዎችም፡፡
- 34. የተሞሉ ብርጭቆዎችም፡፡
- 35. በውስጧ ትርፍ ቃልንም ማስዋሸትንም አይሰሙም፡፡
- 36. ከጌታህ የኾነን ምንዳ በቂ ስጦታን (ተሰጡ)፡፡
- 37. የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ በጣም አዛኝ ከኾነው (ተመነዱ)፡፡ ከእርሱ ጋር መነጋገርን አይችሉም፡፡
- 38. መንፈሱ (ጂብሪል) መላእክቶቹም የተሰለፉ ኾነው በሚቆሙ ቀን አል-ረሕማን ለእርሱ የፈቀደለትና ትክክለኛን ቃል ያለ ሰው ቢኾን እንጅ (መነጋገርን አይችሉም)፡፡
- 39. ይህ የተረጋገጠው ቀን ነው፡፡ የሻም ሰው ወደ ጌታው መመለስን ይይዛል፡፡
- 40. እኛ ሰው ሁሉ እጆቹ ያስቀደሙትን በሚያይበትና ከሓዲውም ዋ ምኞቴ! ምንነው ዐፈር በኾንኩ በሚልበት ቀን ቅርብ የኾነን ቅጣት አስጠነቀቅናችሁ፡፡