80. سورة عبس - ቁርዓን
- 1. ፊቱን አጨፈገገ፤ ዞረም፡፡
- 2. ዕውሩ ስለ መጣው፡፡
- 3. ምን ያሳውቅሃል? (ከኀጢአቶቹ) ሊጥራራ ይከጀላል፡፡
- 4. ወይም ሊገሠጽ ግሠጼይቱም ልትጠቅመው (ይከጀላል)፡፡
- 5. የተብቃቃው ሰውማ፤
- 6. አንተ ለእርሱ (ለእምነቱ በመጓጓት) በፈገግታ ትቀበለዋለህ፡፡
- 7. ባይጥራራ (ባያምን) ባንተ ላይ ምንም የሌለብህ ስትኾን፡፡
- 8. እየገሰገሰ የመጣህ ሰውማ፤
- 9. እርሱ (አላህን) የሚፈራ ሲኾን፤
- 10. አንተ ከእርሱ ትዝዘናጋለህ፡፡
- 11. ተከልከል፡፡ እርሷ ማስገንዘቢያ ናት፡፡
- 12. የሻም ሰው (ቁርኣኑን) ያስታውሰዋል፡፡
- 13. በተከበሩ ጽሑፎች ውስጥ ነው፡፡
- 14. ከፍ በተደረገች ንጹሕ በተደረገች (ጽሑፍ ውስጥ ነው)፡፡
- 15. በጸሐፊዎቹ (መላእክት) እጆች (ንጹሕ የተደረገች)፡፡
- 16. የተከበሩና ታዛዦች በኾኑት (ጸሐፊዎች እጆች)፡፡
- 17. ሰው ተረገመ፤ ምን ከሓዲ አደረገው?
- 18. (ጌታው) በምን ነገር ፈጠረው? (አያስብምን?)
- 19. ከፍትወት ጠብታ ፈጠረው፤ መጠነውም፡፡
- 20. ከዚያም (መውጫ) መንገዱን አገራው፡፡
- 21. ከዚያም ገደለው፤ እንዲቀበርም አደረገው፡፡
- 22. ከዚያም (ማንሳቱን) በሻ ጊዜ ያስነሳዋል፡፡
- 23. በእውነት ያንን (ጌታው) ያዘዘውን ገና አልፈጸመም፡፡
- 24. ሰውም ወደ ምግቡ ይመልከት፡፡
- 25. እኛ ውሃን ማንቧቧትን ያንቧቧን መኾናችንን፡፡
- 26. ከዚያም ምድርን (በደካማ ቡቃያ) መሰንጠቅን የሰነጠቅን፤
- 27. በውስጧም እኽልን ያበቀልን፤
- 28. ወይንንም፤ እርጥብ ያበቀልን፤
- 29. የዘይት ወይራንም ዘንባባንም፤
- 30. ጭፍቆች አትክልቶችንም፤
- 31. ፍራፍሬንም ገለባንም፤ (ያበቀልን መኾናችንን ይመልከት)፡፡
- 32. ለእናንተም ለእንስሶቻችሁም መጠቀሚያ ይኾን ዘንድ (ይህን ሠራን)፡፡
- 33. አደንቋሪይቱም (መከራ) በመጣች ጊዜ፤
- 34. ሰው ከወንድሙ በሚሸሽበት ቀን፤
- 35. ከናቱም ካባቱም፤
- 36. ከሚስቱም ከልጁም፤
- 37. ከእነርሱ ለየሰው ሁሉ በዚያ ቀን (ከሌላው) የሚያብቃቃው ኹነታ አልለው፡፡
- 38. ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው፤
- 39. ሳቂዎችም ተደሳቾችም ናቸው፡፡
- 40. ፊቶችም በዚያ ቀን በላያቸው ላይ ትቢያ አልለባቸው፤
- 41. ጥቁረት ትሸፍናቸዋለች፤
- 42. እነዚያ እነሱ ከሓዲዎቹ አመጸኞቹ ናቸው፡፡