32. سورة السجدة - ቁርዓን
- 1. አ.ለ.መ (አሊፍ ላም ሚም)፡፡
- 2. የመጽሐፉ መወረድ ጥርጥር የለበትም፡፡ ከዓለማት ጌታ ነው፡፡
- 3. ይልቁንም «ቀጠፈው» ይላሉን? አይደለም፡፡ እርሱ ከጌታህ ዘንድ የሆነ እውነት ነው፡፡ በእርሱ ከአንተ በፊት ከአስፈራሪ (ነቢይ) ያልመጣባቸውን ሕዝቦች ልታስፈራራበት (ያወረደልህ ነው)፡፡ እነርሱ ሊምመሩ ይከጀላልና፡፡
- 4. አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸውም ያለውን ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ስልጣኑ) የተደላደለ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም፤ አትገሰጹምን?
- 5. ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ከምትቆጥሩት (ዘመን) ልኩ ሺህ ዓመት በሆነ ቀን ውስጥ ወደርሱ ይወጣል (ይመለሳል)፡፡
- 6. ይህ (ይህንን የሠራው) ሩቁንም ቅርቡንም ሁሉ ዐዋቂው አሸናፊው፣ አዛኙ (ጌታ) ነው፡፡
- 7. ያ የፈጠረውን ነገር ሁሉ ያሳመረው የሰውንም ፍጥረት ከጭቃ የጀመረው ነው፡፡
- 8. ከዚያም ዘሮቹን ከተንጣለለ፣ ከደካማ ውሃ ያደረገ ነው፡፡
- 9. ከዚያም (ቅርጹን) አስተካከለው፡፡ በእርሱ ውስጥም ከመንፈሱ ነፋበት፤ (ነፍስ ዘራበት)፡፡ ለእናንተም ጆሮዎችን፣ ዓይኖችንና ልቦችንም አደረገላችሁ፡፡ በጣም ጥቂትን ብቻ ታመሰግናላችሁ፡፡
- 10. «በምድርም ውስጥ (በስብሰን) በጠፋን ጊዜ እኛ በአዲስ መፈጠር ውስጥ እንሆናለን?» አሉ፡፡ በእውነቱ እነርሱ በጌታቸው መገናኘት ከሓዲዎች ናቸው፡፡
- 11. «በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችኋል፡፡ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ» በላቸው፡፡
- 12. አመጸኞችም በጌታቸው ዘንድ ራሶቻቸውን ያቀረቀሩ ሆነው «ጌታችን ሆይ! አየን፣ ሰማንም፡፡ መልካምን እንሠራለንና (ወደ ምድረ ዓለም) መልሰን፡፡ እኛ አረጋጋጮች ነን፡፡» (የሚሉ ሲሆኑ) ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር)፡፡
- 13. በሻንም ኖሮ ነፍስን ሁሉ ቅንነቷን (እምነቷን) በሰጠናት ነበር፡፡ ግን ገሀነምን ከአጋንንትና ከሰዎች የተሰበሰቡ ሆነው በእርግጥ እሞላለሁ ማለት ቃሉ ከእኔ ተረጋግጧል፡፡
- 14. ይህንንም ቀናችሁን መገናኘትን በመርሳታችሁ ምክንያት (ቅጣትን) ቅመሱ! እኛ ተውናችሁ፡፡ ትሠሩት በነበራችሁትም ጥፋት ዘውታሪን ቅጣት ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡
- 15. በአንቀጾቻችን የሚያምኑት እነዚያ በእርሷ በተገሰጹ ጊዜ ሰጋጆች ሆነው የሚወድቁትና እነርሱም የማይኮሩ ሆነው በጌታቸው ምስጋና (ተጎናጽፈው) የሚያወድሱት ብቻ ናቸው፡፡
- 16. ጌታቸውን ለመፍራትና ለመከጀል የሚጠሩት ሆነው ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ፡፡ ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለገሳሉ፡፡
- 17. ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም፡፡
- 18. አማኝ የሆነ ሰው አመጸኛ እንደ ሆነ ሰው ነውን? አይስተካከሉም፡፡
- 19. እነዚያ ያመኑና መልካሞችን የሰሩማ ለእነርሱ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መስተንግዶ ሲሆኑ መኖሪያ ገነቶች አሏቸው፡፡
- 20. እነዚያ ያመጹትማ፤ መኖሪያቸው እሳት ናት፡፡ ከእርሷ መውጣትን በፈለጉ ቁጥር በእርሷ ውስጥ ይመለሳሉ፡፡ ለእነርሱም «ያንን በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» ይባላሉ፡፡
- 21. ይመለሱ ዘንድም ከትልቁ ቅጣት በፊት (በዚህ ዓለም) ከትንሹ ቅጣት በእርግጥ እናቀምሳቸዋለን፡፡
- 22. በጌታውም አንቀጾች ከተገሰጸና ከዚያም ከተዋት ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? (የለም)፤ እኛ ከተንኮለኞቹ ተበቃዮች ነን፡፡
- 23. ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ እርሱን ከመገናኘትህም በመጠራጠር ውስጥ አትሁን፡፡ ለእስራኤል ልጆችም መሪ አደረግነው፡፡
- 24. በታገሱና በተዓምራቶቻችን የሚያረጋግጡ በሆኑም ጊዜ ከእነርሱ በትዕዛዛችን የሚመሩ መሪዎች አደረግን፡፡
- 25. ጌታህ እርሱ በዚያ በእርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው (በፍርድ) ይለያል፡፡
- 26. ከክፍለ ዘመናት ሰዎች ብዙዎችን ያጠፋን መሆናችን በመኖሪያዎቻቸው የሚሄዱ ሲሆኑ ለእነርሱ አልተገለፀላቸውምን? በዚህ ውስጥ ምልክቶች አሉት፤ አይሰሙምን?
- 27. እኛ ውሃን ወደ ደረቅ ምድር የምንነዳ እንስሶቻቸውና ነፍሶቻቸው ከእርሱ የሚበሉለትንም አዝመራ በእርሱ የምናወጣ መኾናችንን አያዩምን? አይመለከቱምን?
- 28. «ከእውነተኞችም እንደሆናችሁ ይህ ፍርድ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡
- 29. «በፍርድ ቀን እነዚያን የካዱትን ሰዎች እምነታቸው አይጠቅማቸውም፡፡ እነርሱም ጊዜን አይሰጡም፤» በላቸው፡፡
- 30. እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ተጠባበቅም፤ እነርሱ ተጠባባቂዎች ናቸውና፡፡