15. سورة الحجر - ቁርዓን
- 1. አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ) ይህች (አናቅጽ) ከመጽሐፉ አንቀጾችና ገላጭ ከኾነው ቁርኣን ናት፡፡
- 2. እነዚያ የካዱት (በትንሣኤ ቀን) ሙስሊሞች በኾኑ ኖሩ በብዛት ይመኛሉ፡፡
- 3. ተዋቸው ይብሉ፤ ይጠቀሙም፡፡ ተስፋም ያዘናጋቸው፡፡ በእርግጥም (መጥፎ ፍጻሜያቸውን) ያውቃሉ፡፡
- 4. ማንኛይቱንም ከተማ ለእርሷ የተወሰነ መጽሐፍ (ጊዜያት) ያላት ኾና እንጂ አላጠፋንም፡፡
- 5. ማንኛይቱም ሕዝብ ጊዜዋን ምንም አትቀድምም፡፡ (ከእርሱ) አይቆዩምም፡፡
- 6. «አንተ ያ በእርሱ ላይ ቁርኣን የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ ዕብድ ነህ» አሉም፡፡
- 7. «ከእውነተኞቹ እንደ ኾንክ በመላእክት (መስካሪ) ለምን አትመጣንም» (አሉ)፡፡
- 8. መላእክትን በእውነት (በቅጣት) እንጂ አናወርድም፡፡ ያን ጊዜም የሚቆዩ አይደሉም፡፡
- 9. እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡
- 10. ከአንተም በፊት በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ሕዝቦች ውስጥ (መልክተኞችን) በእርግጥ ልከናል፡፡
- 11. ማንኛውም መልእክተኛ በእርሱ የሚያላግጡበት ኾነው እንጅ አይመጣቸውም ነበር፡፡
- 12. እንደዚሁ (ማስተባበልን) በአመጸኞቹ ልቦች ውስጥ እናገባዋለን፡፡
- 13. በእርሱ አያምኑበትም፡፡ የቀድሞዎቹም ድርጊት በእርግጥ አልፋለች፤ (እንደጠፉ ይጠፋሉ)፡፡
- 14. በእነርሱም ላይ ከሰማይ ደጃፍን በከፈትንላቸውና በእርሱ ሲወጡ በዋሉ ኖሮ፤
- 15. «የተዘጉት ዓይኖቻችን ናቸው፡፡ እንዲያውም እኛ የተደገመብን ሰዎች ነን» ባሉ ነበር፡፡
- 16. በሰማይም ላይ ቡርጆችን በእርግጥ አድርገናል፡፡ ለተመልካቾችም (በከዋክብት) አጊጠናታል፡፡
- 17. ከተባረረ ሰይጣንም ሁሉ ጠብቀናታል፡፡
- 18. ግን (ወሬ) መስማትን የሚሰርቅ ወዲየውኑ አብሪ ችቦ ይከተለዋል፡፡ (ያቃጥለዋል)፡፡
- 19. ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በውስጧም ኮረብታዎችን ጣልናባት፡፡ በውስጧም (የተለካን) በቃይ ሁሉ አበቀልንባት፡፡
- 20. በእርሷም ውስጥ ለእናንተ መኖሪያዎችንና ለእርሱ መጋቢዎቹ ያልኾናችሁትንም (እንስሳትን) አደረግንላችሁ፡፡
- 21. መካዚኖቹም (መክፈቻቸው) እኛ ዘንድ ያልሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ በተወሰነም ልክ እንጂ አናወርደውም፡፡
- 22. ነፋሶችንም (ደመናን) ተሸካሚዎች አድርገን ላክን፡፡ ከሰማይም (ከደመና) ዝናብን አወረድን፡፡ እርሱንም አጠጣናችሁ፡፡ እናንተም ለእርሱ አድላቢዎች አይደላችሁም፡፡
- 23. እኛም ሕያው የምናደርግና የምንገድል እኛው ብቻ ነን፡፡ እኛም (ፍጡርን ሁሉ ) የምንወርስ (ቀሪ) ነን፡፡
- 24. ከእናንተም ተቀዳሚዎቹን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ ወደ ኋላም ቀሪዎቹን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡
- 25. ጌታህም እርሱ ይሰበስባችኋል፡፡ እርሱ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡
- 26. ሰውንም ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጥቁር ጭቃ በእርግጥ ፈጠርነው፡፡
- 27. ጃንንም (ከሰው) በፊት ከእሳት ነበልባል ፈጠርነው፡፡
- 28. ጌታህም ለመላእክት ባለጊዜ (አስታውስ)፡፡ እኔ ሰውን ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጭቃ እፈጥራለሁ፡፡
- 29. (ፍጥረቱን) ባስተካከልኩትና በውስጡ ከመንፈሴ በነፋሁበትም ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ፡፡
- 30. መላእክትም መላውም ተሰብስበው ሰገዱ፡፡
- 31. ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር፡፡ ከሰጋጆቹ ጋር ከመኾን እንቢ አለ፡፡
- 32. (አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! ከሰጋጆቹ ጋር የማትኾን ላንተ ምን ምክንያት አለህ» አለው፡፡
- 33. «ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከግም ጭቃ ለፈጠርከው ሰው ልሰግድ አይገባኝም» አለ፡፡
- 34. (አላህ) አለው «ከርሷም ውጣ፡፡ አንተ የተባረርክ እርጉም ነህና፡፡»
- 35. «ባንተ ላይም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ እርግማን አለብህ፡፡»
- 36. «ጌታዬ ሆይ! እንግዲውያስ (ሰዎች) እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ አቆየኝ» አለ፡፡
- 37. (አላህም) አለ «አንተ ከሚቆዩት ነህ፡፡
- 38. «እስከታወቀው ወቅት ቀን ድረስ፡፡»
- 39. (ኢብሊስ) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔን በማጥመምህ ይኹንብኝ ለነርሱ በምድር ላይ (ኀጢአትን) እሸልምላቸዋለሁ፡፡ ሁሉንም አጠማቸዋለሁም፡፡»
- 40. «ከነርሱ ፍጹሞቹ ባሮችህ ብቻ ሲቀሩ፡፡»
- 41. (አላህም) አለ «ይህ በእኔ ላይ (መጠበቁ የተገባ) ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»
- 42. «እነሆ ባሮቼ በእነሱ ላይ ላንተ ስልጣን የለህም፡፡ ከጠማሞቹ የተከተለህ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡»
- 43. «ገሀነምም (ለርሱና ለተከተሉት) ለመላውም በእርግጥ ቀጠሯቸው ናት፡፡
- 44. «ለእርሷ ሰባት ደጃፎች አሏት፡፡ ለየደጀፉም ሁሉ ከእነሱ የተከፈለ ፋንታ አለ፡፡
- 45. «እነዚያ (ከኀጢአት) የተጠነቀቁት በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡
- 46. «ጸጥተኞች ኾናችሁ በሰላም ግቧት (ይባላሉ)፡፡
- 47. «ባልጋዎችም ላይ ፊት ለፊት የሚቅጣጩ ወንድማማቾች ኾነው በደረቶቻቸው ውስጥ ከቂም ያለውን ሁሉ እናስወግዳለን፡፡
- 48. «በእርሷም ውስጥ ድካም አይነካቸውም፡፡ እነሱም ከእርሷ የሚወጡ አይደሉም፡፡»
- 49. ባሮቼን እኔ መሓሪው አዛኙ እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡
- 50. ቅጣቴም እርሱ አሳማሚ ቅጣት መኾኑን (ንገራቸው)፡፡
- 51. ከኢብራሂም እንግዶችም (ወሬ) ንገራቸው፡፡
- 52. በእርሱ ላይ በገቡና ሰላም ባሉት ጊዜ የኾነውን (አስታውስ)፡፡ (እርሱም) «እኛ ከእናንተ ፈሪዎች ነን» አላቸው፡፡
- 53. «አትፍራ፤ እኛ ዐዋቂ በኾነ ወንድ ልጅ እናበስርሃለን» አሉት፡፡
- 54. «እርጅና የደረሰብኝ ከመኾኔ ጋር አበሰራችሁኝን በምን ታበስሩኛላችሁ» አለ፡፡
- 55. «በእውነት አበሰርንህ፡፡ ከተሰፋ ቆራጮችም አትኹን» አሉ፡፡
- 56. «ከጠማማዎችም በስተቀር ከጌታው እዝነት ተስፋን የሚቆርጥ ማነው» አለ፡፡
- 57. «እናንተ መልክተኞች ሆይ! ኧረ ለመኾኑ ነገራችሁ ምንድን ነው» አለ፡፡
- 58. «እኛ አመጸኞች ወደ ኾኑ ሕዝቦች ተልከናል» አሉት፡፡
- 59. «የሉጥ ቤተሰቦች ብቻ ሲቀሩ፡፡ (እነርሱን) እኛ ሁላቸውንም በእርግጥ የምናድናቸው ነን፡፡
- 60. «ሚስቱ ብቻ ስትቀር፡፡ እርሷን (በቅጣቱ ውስጥ) ከሚቀሩት መኾኗን ወሰነናል» (አሉ)፡፡
- 61. መልክተኞቹም የሉጥን ቤተሰቦች በመጡባቸው ጊዜ፤
- 62. (ሉጥ) «እናንተ የተሳታችሁ ሕዝቦች ናችሁ» አላቸው፡፡
- 63. «አይደለም እኛ ሕዝቦችህ በርሱ ይጠራጠሩበት በነበሩት ቅጣት መጣንህ» አሉት፡፡
- 64. «እውነትንም ይዘን መጣንህ፡፡ እኛም በእርግጥ እውነተኞች ነን፡፡
- 65. ከቤተሰብህም ጋር በሌሊቱ ከፊል ኺድ፡፡ ከኋላቸውም ተከተል፡፡ ከእናንተም አንድም ሰው ወደ ኋላው አይገላመጥ፡፡ ወደ ታዘዛችሁበትም ስፍራ እለፉ» (አሉት)፡፡
- 66. ወደርሱም ያንን ትእዛዝ አወረድን፡፡ (እርሱም) የእነዚህ (ሕዝቦች) መጨረሻ ያነጉ ሲኾኑ (ሥራቸው) መቆረጥ ነው፡፡
- 67. የከተማይቱም ሰዎች የሚበሳሰሩ ኾነው መጡ፡፡
- 68. (ሉጥም) አለ «እነዚህ እንግዶቼ ናቸውና አታጋልጡኝ፡፡
- 69. «አላህንም ፍሩ፤ አታሳፍሩኝም፡፡»
- 70. «ከዓለማት (ማንንም እንዳታስተናግድ) አልከለከልንህምን» አሉት፡፡
- 71. (ሉጥም) «እነኝህ ሴቶች ልጆቼ ናቸው፡፡ ሠሪዎች ብትኾኑ (አግቧቸው)» አለ፡፡
- 72. በዕድሜህ እንምላለን እነሱ በእርግጥ በስከራቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡
- 73. ጩኸቲቱም ፀሐይ የወጣችባቸው ሲኾኑ ያዘቻቸው፡፡
- 74. ላይዋንም ከታችዋ አደረግን፡፡ በእነሱም ላይ የሸክላ ደንጊያዎችን አዘነብንባቸው፡፡
- 75. በዚህ ውስጥ ለተመልካቾች በእርግጥ መገምገሚያዎች አሉበት፡፡
- 76. እሷም (ከተማይቱ) በቀጥታ መንገድ ላይ ናት፡፡
- 77. በዚህ ውስጥ በእርግጥ ለምእምናን መገሰጫ አለ፡፡
- 78. እነሆ የአይከት ሰዎችም በእርግጥ በዳዮች ነበሩ፤
- 79. ከነሱም ተበቀልን ሁለቱም (የሉጥና የአይከት ሕዝቦች ከተሞች) በእርግጥ በግልጽ መንገድ ላይ ናቸው፡፡
- 80. የሒጅርም ሰዎች መልክተኞቹን በእርግጥ አስተባበሉ፡፡
- 81. ተዓምራታችንንም ሰጠናቸው፡፡ ከእርሷም ዘንጊዎች ነበሩ፡፡
- 82. ከኮረብታዎችም ቤቶችን ጸጥተኞች ኾነው ይጠርቡ ነበር፡፡
- 83. ያነጉም ሲኾኑ ጩኸት ያዘቻቸው፤ (ወደሙ)፡፡
- 84. ይሠሩትም የነበሩት ሕንጻ ምንም አልጠቀማቸውም፡፡
- 85. ሰማያትንና ምድርንም በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በእውነት እንጂ (በላግጣ) አልፈጠርንም፡፡ ሰዓቲቱም በእርግጥ መጪ ናት፡፡ መልካምንም ይቅርታ አድርግላቸው፡፡
- 86. ጌታህ እርሱ (ያልነበረን) ፈጣሪው ዐዋቂው ነው፡፡
- 87. ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትንና ታላቁንም ቁርኣን (በሙሉ) በእርግጥ ሰጠንህ፡፡
- 88. ከእነርሱ (ከከሓዲዎች) ብዙዎችን ወገኖች በእርሱ ወደ አጣቀምንበት ጸጋ ዓይኖችህን አትዘርጋ፡፡ በእነሱም ላይ (ባያምኑ) አትዘን፡፡ ክንፍህንም ለምእምናን አለዝብ፡፡
- 89. በልም «እኔ ግልጽ አስፈራሪው እኔ ነኝ፡፡»
- 90. (ሰዎችን ለማገድ የመካን በሮች) በተከፋፈሉት ላይ እንደ አወረድነው (በኾነ ቅጣት አሰፈራሪያችሁ ነኝ በል)፡፡
- 91. (እነርሱም) እነዚያ ቁርኣንንን ክፍልፍሎች ያደረጉ ናቸው፡፡
- 92. በጌታህም እንምላለን፡፡ ሁላቸውንም እንጠይቃቸዋለን፤
- 93. ይሠሩት ከነበሩት ነገር ሁሉ፡፡
- 94. የታዘዝክበትንም ነገር በይፋ ግለጽ፡፡ አጋሪዎችንም ተዋቸው፡፡
- 95. ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንሃል፡፡
- 96. (እነሱም) እነዚያ ከአላህ ጋር ሌላ አምላክን ያደረጉ ናቸው፡፡ በእርግጥም (ፍጻሜያቸውን) ወደፊት ያውቃሉ፡፡
- 97. አንተም በሚሉት ነገር ልብህ የሚጠብ መኾኑን በእርግጥ እናውቃለን፡፡
- 98. ጌታህንም ከማመስገን ጋር አጥራው ከሰጋጆቹም ኹን፡፡
- 99. እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡