76. سورة الانسان - ቁርዓን
- 1. በሰው ላይ የሚታወስ ነገር ሳይኾን ከዘመናት የተወሰነ ጊዜ በእርግጥ አልፎበታል፡፡
- 2. እኛ ሰውን (በሕግ ግዳጅ) የምንሞከረው ስንኾን ቅልቅሎች ከኾኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነው፡፡ ሰሚ ተመልካችም አደረግነው፡፡
- 3. እኛ ወይ አመስጋኝ ወይም ከሓዲ ሲኾን መንገዱን መራነው፤ (ገለጽንለት)፡፡
- 4. እኛ ለከሓዲዎች ሰንሰሎቶችንና እንዛዝላዎችን፣ እሳትንም አዘጋጅተናል፡፡
- 5. በጎ አድራጊዎች መበረዣዋ ካፉር ከኾነች ጠጅ ይጠጣሉ፡፡
- 6. ከእርሷ የአላህ ባሮች የሚጠጡላት (ወደፈለጉበት) ማንቧቧትን የሚያንቧቧት ከኾነች ምንጭ (ይጠጣሉ)፡፡
- 7. (ዛሬ) በስለታቸው ይሞላሉ፡፡ መከራው ተሰራጪ የኾነንም ቀን ይፈራሉ፡፡
- 8. ምግብንም ከመውደዳቸው ጋር ለድኻ፣ ለየቲምም፣ ለምርኮኛም ለእስረኛም ያበላሉ፡፡
- 9. «የምናበላችሁ ለአላህ ውዴታ ብቻ ነው፡፡ ከእናንተ ዋጋንም ማመስገንንም አንፈልግም፡፡
- 10. «እኛ (ፊትን) የሚያጨፈግግን ብርቱ ቀን ከጌታችን እንፈራለንና፤» (ይላሉ)፡፡
- 11. አላህም የዚያን ቀን ክፋት ጠበቃቸው፡፡ (ፊታቸው) ማማርንና መደሰትንም ገጠማቸው፡፡
- 12. በመታገሣቸውም ገነትንና የሐር ልብስን መነዳቸው፡፡
- 13. በውስጧ በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች በውስጧ ፀሐይንም ጨረቃንም የማያዩ ሲኾኑ፡፡
- 14. ዛፎችዋም በእነርሱ ላይ የቀረበች፣ ፍሬዎችዋም (ለለቃሚዎች) መግገራትን የተገራች ስትኾን (ገነትን መነዳቸው)፡፡
- 15. በእነርሱም ላይ ከብር በኾኑ ዕቃዎች (ሰሐኖች) የብርጭቆዎች በኾኑ ኩባያዎችም ይዝዞርባቸዋል፡፡
- 16. መለካትን የለኳቸው በኾኑ የብር ብርጭቆዎች (ይዝዞርባቸዋል)፡፡
- 17. በእርሷም መበረዣዋ ዘንጀቢል የኾነችን ጠጅ ይጠጣሉ፡፡
- 18. በውስጧ ያለችውን ሰልሰቢል ተብላ የምትጠራውን ምንጭ፡፡
- 19. በእነርሱም ላይ (ባሉበት ኹነታ) የሚዘወትሩ ወጣት ልጆች ይዘዋወራሉ፡፡ ባየሃቸው ጊዜ የተበተነ ሉል ናቸው ብለህ ታስባቸዋለህ፡፡
- 20. እዚያም በተመለከትክ ጊዜ ጸጋንና ታላቅ ንግሥናን ታያለህ፡፡
- 21. አረንጓዴዎች የኾኑ የቀጭን ሐር ልብሶችና ወፍራም ሐርም በላያቸው ላይ አልለ፡፡ ከብር የኾኑ አንባሮችንም ይሸለማሉ፡፡ ጌታቸውም አጥሪ የኾነን መጠጥ ያጠጣቸዋል፡፡
- 22. «ይህ በእርግጥ ለእናንተ ዋጋ ኾነ፡፡ ሥራችሁም ምስጉን ኾነ፤» (ይባላሉ)፡፡
- 23. እኛ ቁርኣንን ባንተ ላይ ማውረድን እኛው አወረድነው፡፡
- 24. ለጌታህ ፍርድም ታገሥ፡፡ ከእነርሱም ኀጢአተኛን ወይም ከሓዲን አትታዘዝ፡፡
- 25. የጌታህንም ስም በጧትና ከቀትር በላይ አውሳ፡፡
- 26. ከሌሊቱም ለእርሱ ስገድ፡፡ በረዢም ሌሊትም አወድሰው፡፡
- 27. እነዚያ ፈጣኒቱን ዓለም ይወዳሉ፡፡ ከባድን ቀንም በስተፊታቸው ኾኖ ይተዋሉ፡፡
- 28. እኛ ፈጠርናቸው፡፡ መለያልያቸውንም አጠነከርን፡፡ በሻንም ጊዜ መሰሎቻቸውን መለወጥን እንለውጣለን፡፡
- 29. ይህቺ መገሠጫ ናት፡፡ የሻም ሰው ወደ ጌታው መንገድን ይይዛል፡፡
- 30. አላህም ካልሻ በስተቀር አትሹም፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
- 31. የሚሻውን ሰው በእዝነቱ ውስጥ ያገባዋል፡፡ በዳዮቹንም (ዝቶባቸዋል)፡፡ ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣትን አዘጋጅቶላቸዋል፡፡