62. سورة الجمعة - ቁርዓን
- 1. በሰማያት ያለው በምድርም ያለው ሁሉ ለአላህ ንጉሥ፣ ቅዱስ፣ አሸናፊ፣ ጥበበኛ ለኾነው ያሞግሳል፡፡
- 2. እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርኣንን) በእነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ (ከማጋራት) የሚያጠራቸውም፣ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልክተኛ (ሙሐመድን) ከእነርሱው ውስጥ የላከ ነው፡፡ እነርሱም ከእርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ፡፡
- 3. ከነሱም ሌሎች ገና ያልተጠጉዋቸው በኾኑት ላይ (የላከው ነው)፡፡ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
- 4. ይህ የአላህ ችሮታ ነው፡፡ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፡፡ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡
- 5. የእነዚያ ተውራትን የተጫኑትና ከዚያም ያልተሸከሟት (ያልሠሩባት) ሰዎች ምሳሌ መጽሐፎችን እንደሚሸከም አህያ ብጤ ነው፡፡ የእነዚያ በአላህ አንቀጾች ያስተባበሉት ሕዝቦች ምሳሌ ከፋ፡፡ አላህም በዳዮችን ሕዝቦች አይመራም፡፡
- 6. «እናንተ አይሁዳውያን የኾናችሁ ሆይ! ከሰው ሁሉ በስተቀር እናንተ ብቻ ለአላህ ወዳጆች ነን ብትሉ እውነተኞች እንደኾናችሁ ሞትን ተመኙ» በላቸው፡፡
- 7. እጆቻቸውም ባስቀደሙት ኃጢአት ምክንያት በፍጹም አይመኙትም፡፡ አላህም በዳዮቹን ዐዋቂ ነው፡፡
- 8. «ያ ከእርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው፡፡ ከዚያም ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ወደ ኾነው ጌታ ትመለሳላችሁ፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል» በላቸው፡፡
- 9. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በዐርብ ቀን ለስግደት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማውሳት ኺዱ፡፡ መሸጥንም ተዉ፡፡ ይህ የምታውቁ ብትኾኑ ለእናንተ በጣም የተሻለ ነወ፡፡
- 10. ሶለቲቱም በተፈጸመች ጊዜ በምድር ላይ ተበተኑ፡፡ ከአላህም ችሮታ ፈልጉ፡፡ አላህንም በብዙ አውሱ፡፡ ልትድኑ ይከጀላልና፡፡
- 11. ንግድን ወይም ዛዛታን ባዩ ጊዜም ቆመህ የተዉህ ሲኾኑ ወደእርሷ ይበተናሉ፡፡ አላህ ዘንድ ያለው ዋጋ ከዛዛታም ከንግድም በላጭ ነው፡፡ «አላህም ከሰጪዎቹ ሁሉ ይበልጥ ሲሳይን ሰጭ ነው» በላቸው፡፡