83. سورة المطففين - ቁርዓን
- 1. ለሰላቢዎች ወዮላቸው፡፡
- 2. ለእነዚያ ከሰዎች ባስሰፈሩ ጊዜ የሚያስሞሉ፡፡
- 3. ለእነርሱም (ለሰዎቹ) በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ የሚያጎድሉ (ለኾኑት)፡፡
- 4. እነዚያ እነርሱ ተቀስቃሾች መኾናቸውን አያውቁምን?
- 5. በታላቁ ቀን፡፡
- 6. ሰዎች ሁሉ ለዓለማት ጌታ (ፍርድ)፤ በሚቆሙበት ቀን (ተቀስቃሾች መኾናቸውን)፡፡
- 7. በእውነት የከሓዲዎቹ (የሰላቢዎቹ) መጽሐፍ በእርግጥ በሲጂን ውስጥ ነው፡፡
- 8. ሲጂንም ምን እንደ ኾነ ምን አሳወቀህ?
- 9. የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡
- 10. ለአስተባባዮች በዚያ ቀን ወዮላቸው፡፡
- 11. ለእነዚያ በፍርዱ ቀን ለሚያስተባብሉት፡፡
- 12. በእርሱም ወሰን አላፊ ኀጢአተኛ ሁሉ እንጅ ሌላ አያስተባብልም፡፡
- 13. አንቀጾቻችን በእርሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናቸው» ይላል፡፡
- 14. ይከልከል፤ ይልቁንም በልቦቻቸው ላይ ይሠሩት የነበሩት (ኀጢአት) ደገደገባቸው፡፡
- 15. ይከልከሉ፤ እነርሱ በዚያ ቀን ከጌታቸው (ማየት) ተጋራጆች ናቸው፡፡
- 16. ከዚያም እነርሱ በእርግጥ ገሀነምን ገቢዎች ናቸው፡፡
- 17. ከዚያም «ይህ ያ በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁት ነው» ይባላሉ፡፡
- 18. በእውነቱ የእውነተኞቹ ምእምናን መጽሐፍ በዒሊዮን ውስጥ ነው፡፡
- 19. ዒሊዮንም ምን እንደ ኾነ ምን አሳወቀህ?
- 20. የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡
- 21. ባለሟልዎቹ ይጣዱታል፡፡
- 22. እውነተኞቹ ምእምናን በእርግጥ በድሎት (ገነት) ውስጥ ናቸው፡፡
- 23. በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ኾነው ይመለከታሉ፡፡
- 24. በፊቶቻቸው ላይ የድሎትን ውበት ታውቃለህ፡፡
- 25. ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጠጣሉ፡፡
- 26. ማተሚያው ምስክ ከኾነ፤ በዚህም ተሽቀዳዳሚዎች ይሽቀዳደሙ፡፡
- 27. መበረዣውም ከተስኒም ነው፡፡
- 28. ባለሟሎቹ ከእርሷ የሚጠጡላት ምንጭ ናት፡፡
- 29. እነዚያ ያምመጹት በእነዚያ ባመኑት በእርግጥ ይስቁ ነበሩ፡፡
- 30. በእነርሱም ላይ ባለፉ ጊዜ ይጠቃቀሱ ነበር፡፡
- 31. ወደ ቤተሰቦቻቸውም በተመለሱ ጊዜ (በመሳለቃቸው) ተደሳቾች ኾነው ይመለሱ ነበር፡፡
- 32. ባዩዋቸውም ጊዜ «እነዚህ በእርግጥ ተሳሳቾች ናቸው» ይሉ ነበር፡፡
- 33. በነርሱ ላይ ተጠባባቂዎች ተደርገው ያልተላኩ ሲኾኑ፡፡
- 34. ዛሬ (በትንሣኤ ቀን) እነዚያ ያመኑት በከሓዲዎቹ ይስቃሉ፡፡
- 35. በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ኾነው የሚመለከቱ ሲኾኑ (ይስቃሉ)፡፡
- 36. ከሓዲዎች ይሠሩት የነበሩትን (ዋጋ) ተመነዱን? (ይላሉ)፡፡