52. سورة الطور - ቁርዓን
- 1. በጡር (ጋራ) እምላለሁ፡፡
- 2. በተጻፈው መጽሐፍም፡፡
- 3. በተዘረጋ ብራና ላይ፤ (በተጻፈው)፡፡
- 4. በደመቀው ቤትም፡፡
- 5. ከፍ በተደረገው ጣራም፡፡
- 6. በተመላው ባሕርም እምላለሁ፡፡
- 7. የጌታህ ቅጣት በእርግጥ ወዳቂ ነው፤ (የማይቀር ነው)፡፡
- 8. ለእርሱ ምንም ገፍታሪ የለውም፡፡
- 9. ሰማይ ብርቱ መዞርን በምትዞርበት ቀን (ይኾናል)፡፡
- 10. ተራራዎችም መኼድን በሚኼዱበት (ቀን)፡፡
- 11. ለአስተባባዮችም ያን ጊዜ ወዮላቸው፡፡
- 12. ለእነዚያ እነርሱ በውሸት ውስጥ የሚጫወቱ ለኾኑት፡፡
- 13. ወደ ገሀነም እሳት በኀይል መግገፍተርን በሚግገፈተሩበት ቀን፡፡
- 14. ይህቺ ያቺ በእርሷ ታስተባብሉባት የነበራችሁት እሳት ናት፡፡
- 15. ይህ (ፊት ትሉ እንደነበራችሁት) ድግምት ነውን? ወይስ እናንተ አታዩምን?
- 16. ግቧት ታገሱም ወይም አትታገሡ በእናንተ ላይ እኩል ነው፡፡ የምትምመነዱት ትሠሩት የነበራችሁትን (ፍዳ) ብቻ ነው (ይባላሉ)፡፡
- 17. አላህን ፈሪዎቹ በእርግጥ በገነቶችና በጸጋ ውስጥ ናቸው፡፡
- 18. ጌታቸው በሰጣቸው ጸጋ ተደሳቾች ኾነው (በገነት ውስጥ ናቸው)፡፡ የገሀነምንም ስቃይ ጌታቸው ጠበቃቸው፡፡
- 19. «ትሠሩት በነበራችሁት ምክንያት ተደሳቾች ኾናችሁ ብሉ፤ ጠጡም፤» (ይባላሉ)፡፡
- 20. በተደረደሩ አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ኾነው (በገነት ይኖራሉ)፡፡ ዓይናማዎች በኾኑ ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን፡፡
- 21. እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው ዝርያቸውን በእነርሱ እናስጠጋለን፡፡ ከሥራቸውም ምንም አናጎድልባቸውም፡፡ ሰው ሁሉ በሠራው ሥራ ተያዢ ነው፡፡
- 22. ከሚሹትም ሁሉ እሸትንና ስጋን እንጨምርላቸዋለን፡፡
- 23. በውስጧ መጠጥን ይሰጣጣሉ፡፡ በውስጧ ውድቅ ንግግርና መውወንጀልም የለም፡፡
- 24. ለነርሱም የኾኑ ወጣቶች ልክ የተሸፈነ ሉል መስለው በእነርሱ ላይ (ለማሳለፍ) ይዘዋወራሉ፡፡
- 25. የሚጠያየቁ ኾነውም ከፊላቸው በከፊሉ ላይ ይዞራል፡፡
- 26. «እኛ ፊት በቤተሰቦቻችን ውስጥ (ከቅጣት) ፈሪዎች ነበርን» ይላሉ፡፡
- 27. «አላህም በእኛ ላይ ለገሰ፡፡ የመርዛም እሳት ቅጣትንም ጠበቀን፡፡
- 28. «እኛ ከዚህ በፊት እንለምነው ነበርን፡፡ እነሆ እርሱ በጎ ዋይ አዛኝ ነውና» (ይላሉ)፡፡
- 29. (ሰዎችን) አስታውስም፡፡ አንተም በጌታህ ጸጋ ምክንያት ጠንቋይም ዕብድም አይደለህም፡፡
- 30. ይልቁንም የሞትን አደጋ በእርሱ የምንጠባበቅበት የኾነ ባለ ቅኔ ነው ይላሉን?
- 31. «ተጠባበቁ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ከሚጠባበቁት ነኝ» በላቸው፡፡
- 32. አእምሮዎቻቸው በዚህ ያዟቸዋልን? አይደለም በእውነቱ እነርሱ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦች ናቸው፡፡
- 33. ወይም «ቀጠፈው ይላሉን?» አይደለም፤ በእውነቱ አያምኑም፡፡
- 34. እውነተኞችም ቢኾኑ መሰሉ የኾነን ንግግር ያምጡ፡፡
- 35. ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?
- 36. ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም፡፡
- 37. ወይስ የጌታህ ግምጃ ቤቶች እነርሱ ዘንድ ናቸውን? ወይስ እነርሱ አሸናፊዎች ናቸውን?
- 38. ወይስ ለእነርሱ በእርሱ ላይ (ከሰማይ) የሚያዳምጡበት መሰላል አላቸውን? አድማጫቸውም (ሰማሁ ቢል) ግልጽን አስረጅ ያምጣ፡፡
- 39. ወይስ ለእርሱ ሴቶች ልጆች አሉትን? ለእናንተም ወንዶች ልጆች አሏችሁን?
- 40. ወይስ ዋጋን ትጠይቃቸዋለህን? ስለዚህ እነርሱ ከዕዳው የተከበዱ ናቸውን?
- 41. ወይስ ሩቁ ምስጢር እነርሱ ዘንድ ነውን? ስለዚህ እነርሱ ይጽፋሉን?
- 42. ወይስ ተንኮልን (ባንተ) ይሻሉን? እነዚያም የካዱት እነርሱ በተንኮል ተሸናፊዎች ናቸው፡፡
- 43. ወይስ ለእነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ አላቸውን? አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ፡፡
- 44. ከሰማይም ቁራጭን (በእነርሱ ላይ) ወዳቂ ኾኖ ቢያዩ ኖሮ «ይህ የተደራረበ ደመና ነው» ይሉ ነበር፡፡
- 45. ያንንም በእርሱ የሚግገደሉበትን ቀናቸውን እስከሚገናኙ ድረስ ተዋቸው፡፡
- 46. ተንኮላቸው ከእነርሱ ምንንም የማይጠቅማቸውንና እነርሱም የማይርረዱበትን ቀን (እስከ ሚገናኙ ተዋቸው)፡፡
- 47. ለእነዚያ ለበደሉትም ከዚህ ሌላ ቅርብ ቅጣት አልላቸው፡፡ ግን አብዛኛዎቻቸው አያውቁም፡፡
- 48. ለጌታህ ፍርድም ታገሥ፡፡ አንተ በጥበቃችን ውስጥ ነህና፡፡ ጌታህንም በምትነሳ ጊዜ ከማመስገን ጋር አወድሰው፡፡
- 49. ከሌሊቱም አወድሰው፡፡ በከዋክብት መዳበቂያ ጊዜም (ንጋት ላይ አወድሰው)፡፡