69. سورة الحاقة - ቁርዓን
- 1. እውነትን አረጋጋጪቱ (ትንሣኤ)፡፡
- 2. አረጋጋጪቱም (እርሷ) ምንድን ናት!
- 3. አረጋጋጪቱም ምን እንደኾነች ምን አሳወቀህ?
- 4. ሰሙድና ዓድ በቆርቋሪይቱ (ትንሣኤ) አስተባበሉ፡፡
- 5. ሠሙድማ ወሰን በሌላት ጩኸት ተጠፋ፤ (ተወደሙ)፡፡
- 6. ዓድማ በኀይል በምትንሻሻ ብርቱ ነፋስ ተጠፉ፡፡
- 7. ተከታታይ በኾኑ ሰባት ሌሊቶችና ስምንት መዓልቶች ውስጥ በእነርሱ ላይ ለቀቃት፡፡ ሕዝቦቹንም፤ በውስጧ የተጣሉ ኾነው ልክ ክፍት የኾኑ የዘንባባ ግንዶች መስለው ታያቸዋለህ፡፡
- 8. ለእነርሱም ቀሪን ታያለህን?
- 9. ፈርዖን ከበፊቱ የነበሩትም ሰዎች ተገልባጮቹም (ከተሞች) በኀጢአት (ሥራዎች) መጡ፡፡
- 10. የጌታቸውንም መልእክተኛ ትዕዛዝ ጣሱ፡፡ የበረታችንም አያያዝ ያዛቸው፡፡
- 11. እኛ ውሃው ባየለ ጊዜ በተንሻላይቱ ታንኳ ውስጥ ጫንናችሁ፡፡
- 12. ለእናንተ መገሰጫ ልናደርጋት አጥኒ የኾነችም ጆሮ ታጠናት ዘንድ፡፡
- 13. በቀንዱም አንዲት መንነፋት በተነፋች ጊዜ፡፡
- 14. ምድርና ጋራዎችም (ከስፍራቸው) በተነሱና አንዲትን መሰባበር በተሰባበሩ ጊዜ፡፡
- 15. በዚያ ቀን ኋኝቱ (ትንሣኤ) ትኾናለች፡፡
- 16. ሰማይም ትቀደዳለች፡፡ ስለዚህ እርሷ በዚያ ቀን ደካማ ናት፡፡
- 17. መላእክትም በየጫፎችዋ ላይ ይኾናሉ፡፡ የጌታህንም ዐርሽ በዚያ ቀን ስምንት መላእክት ከበላያቸው ይሸከማሉ፡፡
- 18. በዚያ ቀን ከእናንተ ተደባቂ (ነገሮች) የማይደበቁ ሲኾኑ ትቅቀረባላችሁ፡፡
- 19. መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ (ለጓደኞቹ) «እንኩ፤ መጽሐፌን አንብቡ» ይላል፡፡
- 20. «እኔ ምርመራየን የምገናኝ መኾኔን አረጋገጥኩ፤» (ተዘጋጀሁም ይላል)፡፡
- 21. እርሱም በተወደደች ኑሮ ውሰጥ ይኾናል፡፡
- 22. በከፍተኛይቱ ገነት ውስጥ፡፡
- 23. ፍሬዎችዋ ቅርቦች የኾኑ፡፡
- 24. በአለፉት ቀናት ውስጥ (በምድረ ዓለም) ባስቀደማችሁት ምክንያት ብሉ፤ ጠጡም፤ (ይባላሉ)፡፡
- 25. መጽሐፉንም በግራው የተሰጠማ «ዋ ጥፋቴ! ምነው መጽሐፌን ባልተሰጠሁ» ይላል፡፡
- 26. «ምርመራየንም ምን እንደኾነ ባላወቅኩ፡፡
- 27. «እርሷ (ሞት ሕይወቴን) ምነው ፈጻሚ በኾነች፡፡
- 28. «ገንዘቤ ከእኔ ምንንም አላብቃቃኝ፤ (አልጠቀመኝም)፡፡
- 29. «ኀይሌ ከእኔ ላይ ጠፋ» (ይላል)፡፡
- 30. «ያዙት፤ እሰሩትም፡፡
- 31. «ከዚያም በእሳት ውሰጥ አግቡት፡፡
- 32. «ከዚያም ርዝመቷ ሰባ ክንድ በኾነች ሰንሰለት ውስጥ አግቡት፡፡»
- 33. እርሱ ታላቅ በኾነው አላህ አያምንም ነበርና፡፡
- 34. ድኾችንም በማብላት ላይ አያግባባም ነበርና፡፡
- 35. ለእርሱም ዛሬ እዚህ ዘመድ የለውም፡፡
- 36. ምግብም ከእሳት ሰዎች ቁስል እጣቢ (እዥ) በስተቀር የለውም፡፡
- 37. ኀጢኣተኞች እንጅ ሌላ አይበላውም፤ (ይባላል)፡፡
- 38. በምታዩትም ነገር እምላለሁ፡፡
- 39. በማታዩትም ነገር፡፡
- 40. እርሱ (ቁርኣን) የተከበረ መልክተኛ ቃል ነው፡፡
- 41. እርሱም የባለቅኔ ቃል (ግጥም) አይደለም፡፡ ጥቂትን ብቻ ታምናላችሁ፡፡
- 42. የጠንቋይም ቃል አይደለም፡፡ ጥቂትን ብቻ ታስታውሳላችሁ፡፡
- 43. ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡
- 44. በእኛ ላይም ከፊልን ቃላት (ያላልነውን) በቀጠፈ ኖሮ፤
- 45. በኀይል በያዝነው ነበር፡፡
- 46. ከዚያም ከእርሱ የልቡን ሥር (የተንጠለጠለበትን ጅማት) በቆረጥን ነበር፡፡
- 47. ከእናንተም ውስጥ ከእርሱ ላይ ከልካዮች ምንም አይኖሩም፡፡
- 48. እርሱም (ቁርኣን) ለጥንቁቆቹ መገሠጫ ነው፡፡
- 49. እኛም ከእናንተ ውስጥ አስተባባዮች መኖራቸውን በእርግጥ እናውቃለን፡፡
- 50. እርሱም (ቁርኣን) በከሓዲዎቹ ላይ ጸጸት ነው፡፡
- 51. እርሱም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡
- 52. የታላቁን ጌታህንም ስም አወድስ፡፡