31. سورة لقمان - ቁርዓን
- 1. አ.ለ.መ. (አሊፍ ላም ሚም)፡፡
- 2. ይህች ጥበብ ከተመላው መጽሐፍ አንቀጾች ናት፡፡
- 3. ለበጎ አድራጊዎች መሪና እዝነት ስትኾን፡፡
- 4. ለእነዚያ ሶላትን አስተካክለው ለሚያደርሱት፣ ዘካንም ለሚሰጡት፣ እነርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም እነርሱ የሚያረጋግጡ ለሆኑት፡፡
- 5. እነዚያ ከጌታቸው በሆነ ቅን መንገድ ላይ ናቸው፡፡ እነዚያም እነርሱ ምኞታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
- 6. ከሰዎችም ያለ ዕውቀት ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስትና ማላገጫ አድርጎ ሊይዛት አታላይ ወሬን የሚገዛ አልለ፡፡ እነዚያ ለእነርሱ አዋራጅ ቅጣት አላቸው፡፡
- 7. አንቀጾቻችንም በእርሱ ላይ በሚነበቡ ጊዜ እንዳልሰማትና በጆሮቹ ድንቁርና እንዳለበት የኮራ ሆኖ ይዞራል፡፡ በአሳማሚ ቅጣትም አብስረው፡፡
- 8. እነዚያ ያመኑና መልካሞችንም የሠሩ ለእነርሱ የጸጋ ገነቶች አሏቸው፡፡
- 9. በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ሲሆኑ፤ አላህም እውነተኛን ተስፋ ቃል ገባላቸው፡፡ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
- 10. ሰማያትን ያለምታዩዋት አዕማድ (ምሰሶዎች) ፈጠረ፡፡ በምድርም ውስጥ በእናንተ እንዳታረገርግ ተራራዎችን ጣለ፡፡ በእርሷም ላይ ከተንቀሳቃሽ ሁሉ በተነ፡፡ ከሰማይም ውሃን አወረድን፡፡ በእርሷም ውስጥ ከመልካም ዓይነት ሁሉ አበቀልን፡፡
- 11. ይህ የአላህ ፍጡር ነው፡፡ እነዚያ ከእርሱ ሌላ ያሉት ምንን እንደፈጠሩ እስኪ አሳዩኝ፡፡ በእውነቱ በዳዮቹ በግልጽ ጥመት ውስጥ ናቸው፡፡
- 12. ለሉቅማንም ጥበብን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ (አልነውም)፡- «አላህን አመስግን፡፡» ያመሰገነም ሰው የሚያመሰግነው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ የካደም ሰው (በራሱ ላይ ነው)፡፡ አላህ ተብቃቂ ምስጉን ነውና፡፡
- 13. ሉቅማንም ለልጁ እርሱ የሚገሥጸው ሲኾን «ልጄ ሆይ! በአላህ (ጣዖትን) አታጋራ፡፡ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና» ያለውን (አስታውስ)፡፡
- 14. ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ) በጥብቅ አዘዝነው፡፡ እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው፡፡ ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው፡፡ ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)፡፡ መመለሻው ወደኔ ነው፡፡
- 15. ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፡፡ በቅርቢቱም ዓለም፤ በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው፡፡ ወደእኔም የተመለሰን ሰው መንገድ ተከተል፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው፡፡ ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ (አልነው)፡፡
- 16. (ሉቅማንም አለ) «ልጄ ሆይ! እርሷ የሰናፍጭ ቅንጣት ክብደት ያህል ብትሆንና በቋጥኝ ውስጥ ወይም በሰማያት ውስጥ ወይም በምድር ውስጥ ብትሆን አላህ ያመጣታል፡፡ አላህ ሩኅሩኅ ውስጥ ዐዋቂ ነውና፡፡
- 17. «ልጄ ሆይ! ሶላትን አስተካክለህ ስገድ፡፡ በበጎ ነገርም እዘዝ፡፡ ከሚጠላም ሁሉ ከልክል፡፡ በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገስ፡፡ ይህ በምር ከሚያዙ ነገሮች ነው፡፡
- 18. «ጉንጭህንም (በኩራት) ከሰዎች አታዙር፡፡ በምድርም ላይ ተንበጥርረህ አትሂድ፡፡ አላህ ተንበጥራሪን ጉረኛን ሁሉ አይወድምና፡፡
- 19. «በአካኼድህም መካከለኛ ኹን፡፡ ከድምጽህም ዝቅ አድርግ፡፡ ከድምጾች ሁሉ አስከፊው የአህዮች ድምጽ ነውና፡፡»
- 20. አላህ በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ ለእናንተ ያገራላችሁ ጸጋዎቹንም ግልጽም ድብቅም ሲኾኑ የሞላላችሁ መኾኑን አታዩምን? ከሰዎችም ያለ ዕውቀትና ያለ መሪ፣ ያለግልጽ መጽሐፍም በአላህ የሚከራከር አልለ፡፡
- 21. ለእነርሱም አላህ ያወረደውን ተከተሉ በተባሉ ጊዜ አይደለም በእርሱ ላይ አባቶቻችንን ያገኘንበትን እንከተላለን ይላሉ፡፡ ሰይጣን ወደ እሳት ቅጣት የሚጠራቸው ቢሆንም (ይከተሉዋቸዋልን?)
- 22. እርሱ መልካም ሠሪ ሆኖ ፊቱን ወደ አላህ የሚሰጥም ሰው ጠንካራን ገመድ በእርግጥ ጨበጠ፡፡ የነገሩም ሁሉ ፍጻሜ ወደ አላህ ነው፡፡
- 23. የካደም ሰው ክህደቱ አያሳዝንህ፡፡ መመለሻቸው ወደኛ ነው፤ የሠሩትንም ሁሉ እንነግራቸዋለን፡፡ አላህ በልቦች ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃልና፡፡
- 24. ጥቂትን እናጣቅማቸዋለን፡፡ ከዚያም ወደ ብርቱ ቅጣት እናስገድዳቸዋለን፡፡
- 25. ሰማያትንና ምድርንም የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ፡፡ ምስጋና ለአላህ ይገባው በላቸው፡፡ ይልቁንም አብዛኛዎቹ አያውቁም፡፡
- 26. በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ አላህ እርሱ ተብቃቂ ምስጉን ነው፡፡
- 27. ከዛፍም በምድር ያለው ሁሉ ብእሮች ቢሆኑ ኖሮ ባሕሩም ከእርሱ (ማለቅ) በኋላ ሰባት ባህሮች የሚጨመሩለት ሆኖ (ቀለም ቢሆንና ቢጻፍባቸው) የአላህ ቃላት ባላለቀች ነበር፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
- 28. እናንተን መፍጠርና እናንተን መቀስቀስ እንደ አንዲት ነፍስ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ አላህ ሰሚ ተመልካች ነውና፡፡
- 29. አላህ ሌሊትን በቀን ውስጥ የሚያስገባ፣ ቀንንም በሌሊት ውስጥ የሚያስገባ፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የገራ መሆኑን አታይምን? ሁሉም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ይሮጣሉ፡፡ አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
- 30. ይህ አላህ እርሱ እውነት ከእርሱም ሌላ የሚግገዙት (ጣዖት) ውሸት በመሆኑና አላህም እርሱ የበላይ ታላቅ በመሆኑ ነው፡፡
- 31. ከአስደናቂ ምልክቶቹ ሊያሳያችሁ መርከቦች በአላህ ችሮታ በባህር ውስጥ የሚንሻለሉ መሆናቸውን አታይምን? በዚህ ውስጥ በጣም ታጋሽ አመስጋኝ ለሆኑ ሁሉ ተዓምራቶች አሉበት፡፡
- 32. እንደ ጥላዎችም የሆነ ማዕበል በሸፈናቸው ጊዜ አላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው ይጠሩታል፡፡ ወደ የብስም ባዳናቸው ጊዜ ከእነሱ ትክክለኛም አልለ፡፡ (ከእነርሱም የሚክድ አለ)፡፡ በአንቀጾቻችንም አታላይ ከዳተኛ ሁሉ እንጂ ሌላው አይክድም፡፡
- 33. እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ፡፡ ወላጅም ከልጁ (በምንም) የማይጠቅምበትን፤ ተወላጅም እርሱ ወላጅን በምንም ጠቃሚ የማይሆንበትን ቀን ፍሩ፡፡ የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና፡፡ ቅርቢቱም ሕይወት አትሸንግላችሁ፡፡ በአላህም (መታገስ) አታላዩ (ሰይጣን) አያታልላችሁ፡፡
- 34. አላህ የሰዓቲቱ ዕውቀት እርሱ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ዝናብንም ያወርዳል፡፡ በማሕፀኖችም ውስጥ ያለን ሁሉ ያውቃል፡፡ ማንኛይቱ ነፍስም ነገ የምትሠራውን አታውቅም፡፡ ማንኛይቱ ነፍስም በየትኛው ምድር እንደምትሞት አታውቅም፡፡ አላህ ዐዋቂ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡