75. سورة القيامة - ቁርዓን
- 1. (ነገሩ ከሓዲዎች እንደሚሉት) አይደለም፡፡ በትንሣኤ ቀን እምላለሁ፡፡
- 2. (ራሷን) ወቃሽ በኾነች ነፍስም እምላለሁ፡፡ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡
- 3. ሰው አጥንቶቹን አለመሰብሰባችንን ያስባልን?
- 4. አይደለም ጣቶቹን (ፊት እንደ ነበሩ) በማስተካከል ላይ ቻዮች ስንኾን (እንሰበስባቸዋለን)፡፡
- 5. ይልቁንም ሰው በፊቱ ባለው ነገር (በትንሣኤ) ሊያስተባብል ይፈልጋል፡፡
- 6. «የትንሣኤው ቀን መቼ ነው?» ሲል ይጠይቃል፡፡
- 7. ዓይንም በዋለለ ጊዜ፡፡
- 8. ጨረቃም በጨለመ ጊዜ፡፡
- 9. ፀሐይና ጨረቃም በተሰበሰቡ ጊዜ፡፡
- 10. «ሰው በዚያ ቀን መሸሻው የት ነው?» ይላል፡፡
- 11. ይከልከል፤ ምንም መጠጊያ የለም፡፡
- 12. በዚያ ቀን መርጊያው ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡
- 13. ሰው በዚያ ቀን ባስቀደመውና ባስቆየው ሁሉ ይነገራል፡፡
- 14. በእርግጥም ሰው በነፍሱ ላይ አስረጅ ነው፡፡ (አካሎቹ ይመሰክሩበታል)፡፡
- 15. ምክንያቶቹን ሁሉ ቢያመጣም እንኳ (አይሰማም)፡፡
- 16. በእርሱ (በቁርኣን ንባብ) ልትቸኩል ምላስህን በእርሱ አታላውስ፡፡
- 17. (በልብህ ውስጥ) መሰብሰቡና ማንበቡ በእኛ ላይ ነውና፡፡
- 18. ባነበብነውም ጊዜ (ካለቀ በኋላ) ንባቡን ተከተል፡፡
- 19. ከዚያም ማብራራቱ በእኛ ላይ ነው፡፡
- 20. (ከመጣደፍ) ተከልከል፡፡ ይልቁንም (ሰዎች) ፈጣኒቱን (ዓለም) ትወዳላችሁ፡፡
- 21. መጨረሻይቱንም (ዓለም) ትተዋላችሁ፡፡ (አትዘጋጁላትም)፡፡
- 22. ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው፡፡
- 23. ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው፡፡
- 24. ፊቶችም በዚያ ቀን ጨፍጋጊዎች ናቸው፡፡
- 25. በርሳቸውም ዐደጋ እንደሚሠራባቸው ያረጋግጣሉ፡፡
- 26. ንቁ (ነፍስ) ብሪዎችን በደረሰች ጊዜ፤
- 27. «አሻሪው ማነው?» በተባለም ጊዜ፡፡
- 28. (ሕመምተኛው) እርሱ (የሰፈረበት ነገር ከዚህ ዓለም) መልለየት መኾኑን ባረጋገጠም ጊዜ፡፡
- 29. ባትም በባት በተጣበቀች ጊዜ፡፡
- 30. በዚያ ቀን መነዳቱ ወደ ጌታህ (ፍርድ) ነው፡፡
- 31. አላመነምም አልሰገደምም፡፡
- 32. ግን አስተባበለ፤ (ከእምነት) ዞረም፡፡
- 33. ከዚያም እየተንጎባለለ ወደ ቤተሰቡ ኼደ፡፡
- 34. የምትጠላውን ነገር (አላህ) ያስከትልህ፡፡ ለአንተ ተገቢህም ነው፡፡
- 35. ከዚያም ጥፋት ይጠጋህ ለአንተ የተገባህም ነው፡፡
- 36. ሰው ስድ ኾኖ መትተውን ይጠረጥራልን?
- 37. የሚፈሰስ ከኾነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን?
- 38. ከዚያም የረጋ ደም ኾነ (አላህ ሰው አድርጎ) ፈጠረውም፡፡ አስተካከለውም፡፡
- 39. ከእርሱም ሁለት ዓይነቶችን ወንድና ሴትን አደረገ፡፡
- 40. ይህ (ጌታ) ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ አይደለምን?