79. سورة النازعات - ቁርዓን
- 1. በኃይል አውጪዎች በኾኑት፤
- 2. በቀስታ መምዘዝንም መዘዦች በኾኑት፤
- 3. መዋኘትም ዋኚዎች በኾኑት፤
- 4. መቅደምንም ቀዳሚዎች በኾኑት፤
- 5. ነገርንም አስተናባሪዎች በኾኑት (መላእክት) እምላለሁ፡፡ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡
- 6. ተርገፍጋፊይቱ (ምድር) በምትርገፈገፍበት ቀን፤
- 7. ለጣቂይቱ የምትከተላት ስትኾን (ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡
- 8. በዚያ ቀን ልቦች ተሸባሪዎች ናቸው፡፡
- 9. ዓይኖቻቸው ተዋራጆች (አቀርቃሪዎች) ናቸው፡፡
- 10. «እኛ ወደ መጀመሪያይቱ ኹነታ ተመላሾች ነን?» ይላሉ፡፡
- 11. «የበሰበሱ አጥንቶች በኾን ጊዜ (እንቀሰቀሳለን?)»
- 12. «ይህቺ ያን ጊዜ ባለ ከሳራ መመለስ ናት» ይላሉ፡፡
- 13. እርሷም አንዲት ጩኸት ብቻ ናት፡፡
- 14. ወዲያውኑም እነርሱ እንቅልፍ በሌለባት (ምድር) ላይ ይኾናሉ፡፡
- 15. የሙሳ ወሬ መጣልህን?
- 16. ጌታው በተቀደሰው ሸለቆ በጡዋ በጠራው ጊዜ፤
- 17. ወደ ፈርዖን ኺድ፡፡ እርሱ ወሰን አልፏልና፡፡
- 18. በለውም፡- «ወደ መጥራራትህ ላንተ (መንገድ) አለህን?»
- 19. «ወደ ጌታህም ልመራህ ትፈራውም ዘንድ፤ (መንገድ አለህን?)» አለው፡፡
- 20. ታላቂቱንም ተዓምር አሳየው፡፡
- 21. አስተባበለም፤ አመጸም፡፡
- 22. ከዚያም (ለማጥፋት) የሚተጋ ኾኖ ዞረ፡፡
- 23. (ሰራዊቶቹን) ሰበሰበም፤ ተጣራም፡፡
- 24. አለም፡- «እኔ ታላቁ ጌታችሁ ነኝ፡፡»
- 25. አላህም በኋለኛይቱና በፊተኛይቱ (ቃል) ቅጣት ያዘው፡፡
- 26. በዚህ ውስጥ ለሚፈራ ሰው በእርግጥ መገምገሚያ አለበት፡፡
- 27. ባፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይንስ ሰማይ? (አላህ) ገነባት፡፡
- 28. ከፍታዋን አጓነ፤ አስተካከላትም፡፡
- 29. ሌሊቷንም አጨለመ፡፡ ቀንዋንም ገለጸ፡፡
- 30. ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት፡፡
- 31. ውሃዋንና ግጦሿን ከእርሷ አወጣ፡፡
- 32. ጋራዎችንም አደላደላቸው፡፡
- 33. ለእናንተና ለእንስሶቻችሁ መጣቀሚያ ይኾን ዘንድ (ይህን አደረገ)፡፡
- 34. ታላቂቱም መዐት በመጣች ጊዜ፣
- 35. ሰው ሁሉ የሠራውን በሚያስታውስበት ቀን፣
- 36. ገሀነምም ለሚያይ ሰው በተገለጠች ጊዜ፣
- 37. የካደ ሰውማ፣
- 38. ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ፣
- 39. ገሀነም እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፡፡
- 40. በጌታው ፊት መቆምን የፈራ ሰውማ ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለ
- 41. ገነት እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት፡፡
- 42. «ከሰዓቲቱ መቼ ነው መኾኛዋ?» ሲሉ ይጠይቁሃል፡፡
- 43. አንተ እርሷን ከማስታወስ በምን ውስጥ ነህ?
- 44. (የዕውቀት) መጨረሻዋ ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡
- 45. አንተ የሚፈራትን ሰው አስፈራሪ ብቻ ነህ፡፡
- 46. እነርሱ በሚያዩዋት ቀን ያንዲት ቀን ምሽትን ወይም ረፏዷን እንጅ ያልቆዩ ይመስላሉ፡፡