51. سورة الذاريات - ቁርዓን
- 1. መበተንን በታኞች በኾኑት (ነፋሶች)፡፡
- 2. ከባድ (ዝናምን) ተሸካሚዎች በኾኑትም (ደመናዎች)፡፡
- 3. ገር (መንሻለልን) ተንሻላዮች በኾኑትም (መርከቦች)፡፡
- 4. ነገርን ሁሉ አከፋፋዮች በኾኑትም (መላእክት) እምላለሁ፡፡
- 5. የምትቀጠሩት (ትንሣኤ) እውነት ነው፡፡
- 6. (እንደየሥራው) ዋጋን ማግኘትም፤ ኋኝ ነው፤ (የማይቀር ነው)፡፡
- 7. የ(ከዋክብት) መንገዶች ባለቤት በኾነችው ሰማይ እምላለሁ፡፡
- 8. እናንተ (የመካ ሰዎች) በተለያየ ቃል ውስጥ ናችሁ፡፡
- 9. ከርሱ የሚዝዞር ሰው ይዝዞራል፡፡
- 10. በግምት የሚናገሩ ውሸታሞች ተረገሙ፡፡
- 11. እነዚያ እነርሱ በሚሸፍን ስሕተተ ውስጥ ዘንጊዎች የኾኑት፡፡
- 12. የዋጋ መስጫው ቀን መቼ እንደ ኾነ ይጠይቃሉ፡፡
- 13. (እነርሱ) በእሳት ላይ በሚፈተኑበት ቀን ነው፡፡
- 14. «መከራችሁን ቅመሱ፤ ይህ ያ በእርሱ ትቻኮሉበት የነበራችሁት ነው» (ይባላሉ)፡፡
- 15. አላህን ፈሪዎቹ በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡
- 16. ያንን ጌታቸው የሰጣቸውን ተቀባዮች ኾነው፤ (በገነት ውስጥ ይኾናሉ)፡፡ እነርሱ ከዚህ በፊት መልካም ሰሪዎች ነበሩና፡፡
- 17. ከሌሊቱ ጥቂትን ብቻ ይተኙ ነበሩ፡፡
- 18. በሌሊቱ መጨረሻዎችም እነርሱ ምሕረትን ይለምናሉ፡፡
- 19. በገንዘቦቻቸውም ውስጥ ለለማኝና (ከልመና) ለተከለከለም (በችሮታቸው) መብት አልለ፡፡
- 20. በምድርም ውስጥ ለሚያረጋግጡ ሰዎች ምልክቶች አልሉ፡፡
- 21. በነፍሶቻችሁም ውስጥ (ምልክቶች አልሉ)፤ ታዲያ አትመለከቱምን?›
- 22. ሲሳያችሁም የምትቀጠሩትም (ፍዳና ምንዳ) በሰማይ ውስጥ ነው፡፡
- 23. በሰማይና በምድር ጌታም እምላለሁ፡፡ እርሱ እናንተ እንደምትናገሩት ብጤ እርግጠኛ ነው፡፡
- 24. የተከበሩት የኢብራሂም እንግዶች ወሬ መጥቶሃልን?
- 25. በእርሱ ላይ በገቡና «ሰለም» ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «ሰላም ያልታወቃችሁ ሕዝቦች ናችሁ፤» አላቸው፡፡
- 26. ወደ ቤተሰቡም ተዘነበለ፤» ወዲያውም የሰባ ወይፈንን አመጣ፡፡
- 27. ወደእነርሱም (አርዶና ጠብሶ) አቀረበው፡፡ «አትበሉም ወይ?» አላቸው፡፡
- 28. ከእነርሱ መፍራትንም በልቡ አሳደረ፡፡ «አትፍራ» አሉት፡፡ በዐዋቂ ወጣት ልጅም አበሰሩት፡፡
- 29. ሚስቱም እየጮኸች መጣች፡፡ ፊቷንም መታች፡፡ «መካን አሮጊት ነኝ» አለችም፡፡
- 30. እንደዚህ ጌታሽ ብሏል፡፡ «እነሆ እርሱ ጥበባ ዐዋቂ ነውና» አሏት፡፡
- 31. «እናንተ መልክተኞች ሆይ! ታዲያ ነገራችሁ ምንድን ነው?» አላቸው፡፡
- 32. (እነርሱም) አሉ፡- «እኛ ወደ አመጸኞች ሕዝቦች ተልከናል፡፡»
- 33. በእነርሱ ላይ ከጭቃ የኾኑን ድንጋዮች ልንለቅባቸው (ተላክን)፡፡
- 34. በጌታህ ዘንድ ለድንበር አላፊዎቹ (በየስማቸው) ምልክት የተደረገባት ስትኾን፡፡
- 35. ከምእምናንም፤ በእርሷ (በከተማቸው) ውስጥ የነበሩትን አወጣን፡፡
- 36. በውስጧም ከሙስሊሞች ከአንድ ቤት (ቤተሰቦች) በስተቀር አላገኘንም፡፡
- 37. በውስጧም ለእነዚያ አሳማሚውን ቅጣት ለሚፈሩት ምልክትን አስቀረን፡፡
- 38. በሙሳም (ወሬ) ውስጥ ወደ ፈርዖን በግልጽ ማስረጃ በላክነው ጊዜ (ምልክትን አደረግን)፡፡
- 39. ከድጋፉ (ከሰራዊቱ) ጋርም (ከእምነት) ዞረ፡፡ (እርሱ) «ድግምተኛ ወይም ዕብድ ነው» አለም፡፡
- 40. እርሱንም ሰራዊቱንም ያዝናቸው፡፡ እርሱ ተወቃሽ ሲኾን በባሕር ውስጥም ጣልናቸው፡፡
- 41. በዓድም በእነርሱ ላይ መካንን ነፋስ በላክን ጊዜ (ምልክት አልለ)፡፡
- 42. በላዩ ላይ የመጣችበትን ማንኛውንም ነገር እንደ በሰበሰ አጥንት ያደረገችው ብትኾን እንጂ አትተወውም፡፡
- 43. በሰሙድም ለእነርሱ «እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ ተጣቀሙ» በተባሉ ጊዜ (ምልክት አልለ)፡፡
- 44. ከጌታቸው ትዕዛዝም ኮሩ፡፡ እነርሱም እያዩ ጩኸት ያዘቻቸው፡፡
- 45. መቆምንም ምንም አልቻሉም፡፡ የሚርረዱም አልነበሩም፡፡
- 46. የኑሕንም ሕዝቦች ከዚህ በፊት (አጠፋን)፡፡ እነርሱ አመጸኞች ሕዝቦች ነበሩና፡፡
- 47. ሰማይንም በኀይል ገነባናት፡፡ እኛም በእርግጥ ቻዮች ነን፡፡
- 48. ምድርንም ዘረጋናት፡፡ ምን ያማርንም ዘርጊዎች (ነን!)
- 49. ትገነዘቡም ዘንድ ከነገሩ ሁሉ ሁለት (ተቃራኒ) ዓይነትን ፈጠርን፡፡
- 50. «ወደ አላህም ሽሹ፤ እኔ ለእናንተ ከርሱ ግልጽ አስጠንቃቂ ነኝና» (በላቸው)፡፡
- 51. ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አታድርጉ፡፡ እኔ ለእናንተ ከእርሱ (የተላክሁ) ግልጽ አስፈራሪ ነኝና፡፡
- 52. (ነገሩ) እንደዚሁ ነው፡፡ እነዚያን ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ከመልክተኛ ማንም አልመጣቸውም፡፡ (እርሱ) «ድግምተኛ ወይም ዕብድ ነው» ያሉ ቢኾኑ እንጂ፡፡
- 53. በእርሱ (በዚህ ቃል) አደራ ተባብለዋልን? አይደለም፤ እነርሱ ጥጋበኞች ሕዝቦች ናቸው፡፡
- 54. ከእነርሱም (ክርክር) ዘወር በል፤ (ተዋቸው)፡፡ አንተ ምንም ተወቃሽ አይደለህምና፡፡
- 55. ገሥጽም፤ ግሣጼ ምእመናንን ትጠቅማለችና፡፡
- 56. ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
- 57. ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፡፡ ሊመግቡኝም አልሻም፡፡
- 58. አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኀይል ባለቤት ነው፡፡
- 59. ለእነዚያም ለበደሉት እንደ ጓደኞቻቸው ፋንታ ብጤ (የቅጣት) ፋንታ አልላቸው፡፡ ስለዚህ አያስቸኩሉኝ፡፡
- 60. ለነዚያም ለካዱት ከዚያ ከሚቀጠሩት ቀናቸው ወዮላቸው፡