26. سورة الشعراء - ቁርዓን
- 1. ጠ.ሰ.መ. (ጧ ሲን ሚም)፡፡
- 2. ይህች ግልጽ ከኾነው መጽሐፍ አንቀጾች ናት፡፡
- 3. አማኞች ባለመኾናቸው፤ (በቁጭት) ነፍስህን ገዳይ መኾን ይፈራልሃል፡፡
- 4. ብንሻ በእነሱ ላይ ከሰማይ ተዓምረን እናወርድና አንገቶቻቸው (መሪዎቻቸው) ለእርሷ ተዋራጆች ይኾናሉ፡፡
- 5. ከአልረሕማንም ዘንድ ኣዲስ የተወረደ ቁርኣን አይመጣላቸውም፤ ከእርሱ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጂ፡፡
- 6. በእርግጥም አስተባበሉ፡፡ የዚያም በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ወሬዎች (ፍጻሜ) ይመጣባቸዋል፡፡
- 7. ወደ ምድርም በውስጧ ከመልካም (በቃይ) ጎሳ ሁሉ ብዙን እንዳበቀልን አላዩምን፡፡
- 8. በዚህ አስደናቂ ምልክት አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- 9. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው፡፡
- 10. ጌታህም ሙሳን «ወደ በደለኞቹ ሕዝቦች ኺድ» በማለት በጠራው ጊዜ (አስታውስ)፡፡
- 11. «ወደ ፈርዖን ሕዝቦች (ኺድ) አላህን አይፈሩምን» (አለው)፡፡
- 12. (ሙሳም) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁ፡፡
- 13. «ልቤም ይጠብባል፡፡ ምላሴም አይፈታም፡፡ ስለዚህ ወደ ሃሩን ላክ፡፡
- 14. «ለእነርሱም በእኔ ላይ (የደም) ወንጀል አልለ፡፡ ስለዚህ እንዳይገድሉኝ እፈራለሁ፡፡»
- 15. (አላህ) አለ «ተው! (አይነኩህም)፡፡ በተዓምራቶቻችንም ኺዱ፡፡ እኛ ከእናንተ ጋር ሰሚዎች ነንና፡፡
- 16. «ወደ ፈርዖንም ኺዱ፡፡ በሉትም፡- እኛ የዓለማት ጌታ መልክተኞች ነን፡፡
- 17. «የእስራኤልን ልጆች ከእኛ ጋር ልቀቅ፡፡»
- 18. (ፈርዖንም) አለ «ልጅ ኾነህ በእኛ ውስጥ አላሳደግንህምን በእኛ ውስጥም ከዕድሜህ ብዙ ዓመታትን አልተቀመጥክምን
- 19. «ያችንም የሠራሃትን ሥራህን አልሠራህምን አንተም ከውለታ ቢሶቹ ነህ» (አለ)፡፡
- 20. (ሙሳም) አለ «ያን ጊዜ እኔም ከተሳሳቱት ኾኜ ሠራኋት፡፡
- 21. «በፈራኋችሁም ጊዜ ከእንናተ ሸሸሁ፡፡ ጌታየም ለእኔ ጥበብን ሰጠኝ፡፡ ከመልክተኞቹም አደረገኝ፡፡
- 22. «ይህችም የእስራኤልን ልጆች ባሪያ በማድረግህ በእኔ ላይ የምትመጻደቅባት ጸጋ ነት፡፡»
- 23. ፈርዖን አለ «(ላከኝ የምትለው) የዓለማትም ጌታ ምንድነው»
- 24. (ሙሳ) «የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ ነው፡፡ የምታረጋግጡ ብትኾኑ (ነገሩ ይህ ነው)፤» አለው፡፡
- 25. (ፈርዖንም) በዙሪያው ላሉት ሰዎች «አትሰሙምን» አለ፡፡
- 26. (ሙሳ) «ጌታችሁና የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው» አለው፡፡
- 27. (ፈርዖን) «ያ ወደእናንተ የተላከው መልክተኛችሁ በእርግጥ ዕብድ ነው» አለ፡፡
- 28. (ሙሳ) «የምሥራቅና የምዕራብ በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ነው፡፡ ታውቁ እንደኾናችሁ (እመኑበት)» አለው፡፡
- 29. (ፈርዖን) «ከእኔ ሌላ አምላክን ብትይዝ በውነቱ ከእስረኞቹ አደርግሃለሁ» አለ፡፡
- 30. (ሙሳ) «በግልጽ አስረጅ ብመጣህም እንኳ» አለው፡፡
- 31. «እንግዲያውስ ከእውነተኞች እንደኾንክ (አስረጁን) አምጣው» አለ፡፡
- 32. በትሩንም ጣለ፡፡ እርሷም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች፡፡
- 33. እጁንም አወጣ፡፡ ወዲያውም እርሷ ለተመልካቾች (የምታበራ) ነጭ ኾነች፡፡
- 34. (ፈርዖን) በዙሪያው ላሉት መማክርት «ይህ በእርግጥ ዐዋቂ ድግምተኛ ነው» አለ፡፡
- 35. «ከምድራችሁ በድግምቱ ሊያወጣችሁ ይፈልጋልና ምንን ታዛላችሁ» (አላቸው)፡፡
- 36. አሉት «እርሱን ወንድሙንም አቆይና በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን ላክ፡፡
- 37. «በጣም ዐዋቂ ድግምተኞችን ሁሉ ያመጡልሃልና፡፡»
- 38. ድግምተኞቹም በታወቀ ቀን ቀጠሮ ተሰበሰቡ፡፡
- 39. ለሰዎቹም «እናንተ ተሰብስባችኋልን» ተባለ፡፡
- 40. «ድግምተኞቹን እነሱ አሸናፊዎች ቢኾኑ እንከተል ዘንድ» (ተባለ)፡፡
- 41. «ድግምተኞቹም በመጡ ጊዜ ለፈርዖን እኛ አሸናፊዎች ብንሆን ለእኛ በእርግጥ ዋጋ አለን» አሉት፡፡
- 42. «አዎን፤ እናንተም ያን ጊዜ ከባለሟሎቹ ትኾናላችሁ» አላቸው፡፡
- 43. ሙሳ «ለእነርሱ እናንተ የምትጥሉትን ጣሉ» አላቸው፡፡
- 44. ገመዶቻቸውንና በትሮቻቸውንም ጣሉ፡፡ «በፈርዖንም ክብር ይኹንብን፡፡ እኛ በእርግጥ አሸናፊዎቹ እኛ ነን» አሉ፡፡
- 45. ሙሳም በትሩን ጣለ፡፡ ወዲያውም እርሷ የሚያስመስሉትን ሁሉ ትውጣለች፡፡
- 46. ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፡፡
- 47. (እነሱም) አሉ «በዓለማት ጌታ አመንን፡፡
- 48. «በሙሳና በሃሩን ጌታ፡፡»
- 49. (ፈርዖንም) «ለእናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለእርሱ አመናችሁን እርሱ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ታላቃችሁ ነው፡፡ ወደፊትም (የሚያገኛችሁን) በእርግጥ ታውቃላችሁ፡፡ እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን (ቀኝና ግራን) በማናጋት እቆረርጣለሁ፡፡ ሁላችሁንም እሰቅላችኋለሁም» አለ፡፡
- 50. (እነርሱም) አሉ «ጉዳት የለብንም፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን፡፡
- 51. «እኛ የምእምናን መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን፡፡»
- 52. ወደ ሙሳም «ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ፡፡ እናንተ የሚከተሉዋችሁ ናችሁና» ስንል ላክን፡፡
- 53. ፈርዖንም በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን (እንዲህ ሲል) ላከ፡፡
- 54. «እነዚህ ጥቂቶች ጭፈሮች ናቸው፡፡
- 55. «እነርሱም ለእኛ አስቆጪዎች ናቸው፡፡
- 56. «እኛም ብዙዎች ጥንቁቆች ነን፤» (አለ)፡፡
- 57. አወጣናቸውም፡፡ ከአትክልቶችና ከምንጮች፡፡
- 58. ከድልቦችም ከመልካም መቀመጫዎችም፡፡
- 59. እንደዚሁ ለእስራኤል ልጆች አወረስናትም፡፡
- 60. ፀሐይዋ ስትወጣም ተከተሉዋቸው፡፡
- 61. ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ የሙሳ ጓዶች «እኛ(የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን» አሉ፡፡
- 62. (ሙሳ) «ተዉዉ! ጌታዬ ከእኔ ጋር ነው፡፡ በእርግጥ ይመራኛል» አለ፡፡
- 63. ወደ ሙሳም «ባሕሩን በበትርህ ምታው» ስንል ላክንበት፡፡ (መታውና) ተከፈለም፡፡ ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ፡፡
- 64. እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን፡፡
- 65. ሙሳንም ከእርሱ ገር ያሉትንም ሰዎች ሁሉንም አዳን፡፡
- 66. ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን፡፡
- 67. በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- 68. ጌታህም እርሱ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 69. በእነሱም (በሕዝቦችህ) ላይ የኢብራሂምን ወሬ አንብብላቸው፡፡
- 70. ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ምንን ትግገዛላችሁ» ባለ ጊዜ፡፡
- 71. «ጣዖታትን እንገዛለን፤ እርሷንም በመገዛት ላይ እንቆያለን» አሉ፡፡
- 72. (እርሱም) አለ «በጠራችኋቸው ጊዜ ይሰሟችኋልን
- 73. «ወይስ ይጠቅሟችኋልን ወይስ ይጎዷችኋልን»
- 74. «የለም! አባቶቻችን እንደዚሁ ሲሠሩ አገኘን» አሉት፡፡
- 75. «ትግገዙት የነበራችሁትን አስተዋላችሁን
- 76. «እናንተም የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁም (የተግገዛችሁትን)፡፡»
- 77. «እነሱም (ጣዖቶቹ) ለእኔ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር (እርሱ ወዳጄ ነው)፡፡
- 78. «(እርሱ) ያ የፈጠረኝ ነው፡፡ እርሱም ይመራኛል፡፡
- 79. «ያም እርሱ የሚያበላኝና የሚያጠጣኝ ነው፡፡
- 80. «በታመምኩም ጊዜ እርሱ ያሽረኛል፡፡
- 81. «ያም የሚገድለኝ ከዚያም ሕያው የሚያደርገኝ ነው፡፡
- 82. ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለእኔ ሊምር የምከጅለው ነው፡፡
- 83. ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትን ስጠኝ! በደጋጎቹም ሰዎች አስጠጋኝ፡፡
- 84. በኋለኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ለእኔ መልካም ዝናን አድርግልኝ፡፡
- 85. የጸጋይቱን ገነት ከሚወርሱትም አድርገኝ፡፡
- 86. ለአባቴም ማር፡፡ እርሱ ከተሳሳቱት ነበረና፡፡
- 87. በሚቀሰቀሱበት ቀንም አታዋርደኝ፡፡
- 88. ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፡፡
- 89. ወደ አላህ በንጹህ ልብ የመጣ ሰው ቢኾን እንጅ፡፡»
- 90. ገነትም ለፈሪዎች በምትቀረብበት (ቀን)፡፡
- 91. ገሀነምም ለጠመሞች በምትገለጽበት (ቀን)፡፡
- 92. ለእነሱም በሚባል ቀን «ትግገዟቸው የነበራችሁት የት ናቸው»
- 93. «ከአላህ ሌላ ሲኾኑ ይረዱዋችኋልን ወይስ (ለራሳቸው) ይርረዳሉን»
- 94. በውስጧም እነሱና ጠማሞቹ በፊቶቻቸው ተጥለው ይንከባለላሉ፡፡
- 95. የሰይጣንም ሰራዊቶች መላውም (ይጣላሉ)፡፡
- 96. እነርሱም በእርሷ ውስጥ የሚከራከሩ ኾነው ይላሉ፡-
- 97. በአላህ እንምላለን፤ እኛ በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነበርን፡፡
- 98. (ጣዖቶቹን) በዓለማት ጌታ ባስተካከልናችሁ ጊዜ፡፡
- 99. አመጸኞቹም እንጅ ሌላ አላሳሳተንም፡፡
- 100. ከአማላጆችም ለእኛ ምንም የለንም፡፡
- 101. አዛኝ ወዳጂም (የለንም)፡፡
- 102. ለእኛም አንዲት ጊዜ መመለስ በኖረችንና ከአማኞቹ በኾን እንመኛለን (ይላሉ)፡፡
- 103. በዚህ ውስጥ አስደናቂ ግሳጼ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- 104. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 105. የኑሕ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባበሉ፡፡
- 106. ወንድማቸው ኑሕ ለእነሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- 107. «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- 108. «አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡
- 109. «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- 110. «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡»
- 111. (እነርሱም) «ወራዶቹ የተከተሉህ ኾነህ ለአንተ እናምናለን» አሉት፡፡
- 112. (እርሱም) አላቸው «ይሠሩት በነበሩት ነገር ምን ዕውቀት አለኝ፡፡
- 113. «ምርመራቸው በጌታዬ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡ ብታውቁ ኖሮ (ይህንን ትርረዱ ነበር)፡፡
- 114. «እኔም አማኞችን አባራሪ አይደለሁም፡፡
- 115. «እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም፡፡»
- 116. «ኑሕ ሆይ! (ከምትለው) ባትከለከል በእርግጥ ከሚወገሩት ትኾናለህ» አሉት፡፡
- 117. (እርሱም) አለ «ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ አስተባበሉኝ፡፡
- 118. «በእኔና በእነርሱም መካከል (ተገቢ) ፍርድን ፍረድ፡፡ አድነኝም፡፡ ከእኔ ጋር ያሉትንም ምእምናን፡፡»
- 119. እርሱንም ከእርሱ ጋር ያለውንም ሁሉ በተመላው መርከብ ውስጥ አዳን፡፡
- 120. ከዚያም በኋላ ቀሪዎቹን አሰጠምን፡፡
- 121. በዚህ ውስጥ ታላቅ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም፡፡
- 122. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 123. ዓድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡
- 124. ወንድማቸው ሁድ ለነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- 125. «እኔ ለናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- 126. «አላህንም ፍሩ ታዘዙኝም፡፡
- 127. «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- 128. «የምትጫወቱ ኾናችሁ በከፍተኛ ስፍራ ሁሉ ላይ ምልክትን ትገነባላችሁን
- 129. «የውሃ ማጠራቀሚያዎችንና ሕንፃዎችንም ዘላለም መኖርን የምትከጅሉ ኾናችሁ ትሠራላችሁን
- 130. «በቀጣችሁም ጊዜ ጨካኞች ኾናችሁ ትቀጣላችሁን
- 131. «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- 132. «ያንንም በምታውቁት (ጸጋ) ያጣቀማችሁን ፍሩ፡፡
- 133. «በእንስሳዎችና በልጆች ያጣቀማችሁን፡፡
- 134. «በአትክልቶችና በምንጮችም፡፡
- 135. «እኔ በእናንተ ላይ የታላቅን ቀን ቅጣት እፈራለሁና፡፡»
- 136. (እነርሱም) አሉ «ብትገስጽም ወይም ከገሳጮቹ ባትኾንም በእኛ ላይ እኩል ነው፤ (ያለንበትን አንለቅም)፡፡
- 137. «ይህ የፊተኞቹ ሰዎች ፀባይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
- 138. «እኛም የምንቅቀጣ አይደለንም» (አሉ)፡፡
- 139. አስተባበሉትም፡፡ አጠፋናቸውም፡፡ በዚህም ውስጥ እርግጠኛ ግሳጼ አለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
- 140. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 141. ሰሙድ መልክተኞችን አስተባበለች፡፡
- 142. ወንድማቸው ሷሊህ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- 143. «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- 144. «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- 145. «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- 146. «በዚያ እዚህ ባለው (ጸጋ) ውስጥ የረካችሁ ኾናችሁ ትተዋላችሁን
- 147. «በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ፡፡
- 148. «በአዝመራዎችም ፍሬዋ የበሰለ በኾነች ዘንባባም፤ (ውስጥ ትተዋላችሁን)
- 149. «ብልሆች ኾናችሁ ከጋራዎች ቤቶችንም ትጠርባላችሁ፡፡
- 150. «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- 151. «የወሰን አላፊዎችንም ትዕዛዝ አትከተሉ፡፡
- 152. «የእነዚያን በምድር ላይ የሚያጠፉትንና የማያበጁትን፡፡»
- 153. (እነሱም) አሉ «አንተ በብዙ ከተደገመባቸው ሰዎች ብቻ ነህ፡፡
- 154. «አንተ ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ ከእውነተኞቹም እንደኾንክ ተዓምርን አምጣ፡፡»
- 155. (እርሱም) አለ «ይህች ግመል ናት፡፡ ለእርሷ የመጠጥ ፋንታ አላት፡፡ ለእናንተም የታወቀ ቀን ፋንታ አላችሁ፡፡
- 156. «በክፉም አትንኳት፡፡ የታላቅ ቀን ቅጣት ይይዛችኋልና፡፡»
- 157. ወጓትም፡፡ ወዲያውም ተጸጻቾች ኾነው አነጉ፡፡
- 158. ቅጣቱም ያዛቸው፡፡ በዚህም ውስጥ ግሳፄ አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
- 159. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 160. የሉጥ ሕዝቦች መልክተኞችን አስተባባሉ፡፡
- 161. ወንድማቸው ሉጥ ለእነርሱ ባለ ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- 162. «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- 163. «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- 164. «በእርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልለምናችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- 165. «ከዓለማት ሰዎች ወንዶችን ትመጣላችሁን
- 166. «ከሚስቶቻችሁም ጌታችሁ ለናንተ የፈጠረላችሁን ትተዋላችሁን በእውነቱ እናንተ ወሰን አላፊዎች ሕዝቦ ናችሁ፡፡»
- 167. (እነርሱም) አሉ «ሉጥ ሆይ! ባትከለከል በእርግጥ (ከአገር) ከሚወጡት ትኾናለህ፡፡»
- 168. (እርሱም) አለ «እኔ ሥራችሁን ከሚጠሉት ሰዎች ነኝ፡፡
- 169. «ጌታዬ ሆይ! እኔንም ቤተሰቦቼንም ከሚሠሩት ሥራ (ቅጣት) አድነን፡፡»
- 170. እርሱንም ቤተሰቦቹንም በጠቅላላ አዳንናቸው፡፡
- 171. በቀሪዎቹ ውስጥ የኾነች አሮጊት ብቻ ስትቀር (እርሷ ጠፋች)፡፡
- 172. ከዚያም ሌሎቹን አጠፋን፡፡
- 173. በእነሱም ላይ (የድንጋይን) ዝናምን አዘነምንባቸው፡፡ የተስፈራሪዎቹም ዝናም (ምንኛ) ከፋ፡፡
- 174. በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእመናን አልነበሩም፡፡
- 175. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 176. የአይከት ሰዎች መልክተኞችን አስተባበሉ፤
- 177. ሹዕይብ ለእነርሱ ባላቸው ጊዜ «አትጠነቀቁምን
- 178. «እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝ፡፡
- 179. «አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም፡፡
- 180. «በርሱም ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ ዋጋዬ በዓለማት ጌታ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፡፡
- 181. «ስፍርን ሙሉ፡፡ ከአጉዳዮቹም አትኹኑ፡፡
- 182. «በትክክለኛ ሚዛንም መዝኑ፡፡
- 183. «ሰዎችንም ነገሮቻቸውን አታጉድሉባቸው፡፡ በምድርም ላይ አጥፊዎች ኾናችሁ አታበላሹ፡፡
- 184. «ያንንም የፈጠራችሁን የቀድሞዎቹንም ፍጡሮች (የፈጠረውን) ፍሩ፡፡»
- 185. አሉ «አንተ በብዛት ከተደገመባቸው ሰዎች ነህ፡፡
- 186. «አንተም ብጤያችን ሰው እንጅ ሌላ አይደለህም፡፡ እነሆ ከውሸታሞች ነህ ብለን እንጠረጥርሃለን፡፡
- 187. «ከእውነተኞቹም እንደኾንክ በእኛ ላይ ከሰማይ ቁራጭን ጣልብን፡፡»
- 188. «ጌታዬ የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፤» አላቸው፡፡
- 189. አስተባበሉትም፡፡ የጥላይቷ ቀን ቅጣትም ያዛቸው፡፡ እርሱ የከባድ ቀን ቅጣት ነበርና፡፡
- 190. በዚህ ውስጥ አስደናቂ ተዓምር አልለበት፡፡ አብዛኞቻቸውም ምእምናን አልነበሩም፡፡
- 191. ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡
- 192. እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡
- 193. እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤
- 194. ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡
- 195. ግልጽ በኾነ ዐረብኛ ቋንቋ፡፡
- 196. እርሱም (ቁርኣን) በቀድሞዎቹ መጻሐፍት ውስጥ (የተወሳ ነው)፡፡
- 197. የእስራኤል ልጆች ሊቃውንት የሚያውቁት መኾኑ ለእነርሱ (ለመካ ከሓዲዎች) ምልክት አይኾናቸውምን
- 198. ከአዕጀሞች ባንዱ ላይ ባወረድነውም ኖሮ፤
- 199. በእነርሱ ላይ ባነበበውም በእርሱ አማኞች አይኾኑም ነበር፡፡
- 200. እንደዚሁ (ማስተባበልን) በተንኮለኞች ልቦች ውስጥ አስገባነው፡፡
- 201. አሳማሚ ቅጣትን እስከሚያዩ ድረስ በእርሱ አያምኑም፡፡
- 202. እነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ (ቅጣቱ) ድንገት እስከሚመጣባቸውም ድረስ (አያምኑም)፡፡
- 203. (በመጣባቸው ጊዜ) «እኛ የምንቆይ ነን» እስከሚሉም (አያምኑም)፡፡
- 204. በቅጣታችን ያቻኩላሉን
- 205. አየህን ብዙ ዓመታትን ብናጣቅማቸው፤
- 206. ከዚያም ያ ይስፈራሩበት የነበሩት ቢመጣባቸው፤
- 207. ይጣቀሙበት የነበሩት ሁሉ ከእነሱ ምንም አያብቃቃቸውም፡፡
- 208. አንዲትንም ከተማ ለእርሷ አስፈራሪዎች ያሏት (እና ያስተባበለች) ኾና እንጅ አላጠፋንም፡፡
- 209. (ይህች) ግሳፄ ናት፡፡ በዳዮችም አልነበርንም፡፡
- 210. ሰይጣናትም እርሱን (ቁርኣንን) አላወረዱትም፡፡
- 211. ለእነርሱም አይገባቸውም፤ አይችሉምም፡፡
- 212. እነርሱ (የመላእክትን ንግግር) ከመስማት ተከለከሉ ናቸው፡፡
- 213. ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትግገዛ፤ ከሚቀጡት ትኾናለህና፡፡
- 214. ቅርቦች ዘመዶችህንም አስጠንቅቅ፡፡
- 215. ከምእምናንም ለተከተሉህ ሰዎች ክንፍህን ዝቅ አድርግ፤ (ልዝብ ኹን)፡፡
- 216. «እንቢ» ቢሉህም «እኔ ከምትሠሩት ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡
- 217. አሸናፊ አዛኝ በኾነው (ጌታህ) ላይም ተጠጋ፡፡
- 218. በዚያ ለሶላት በምትቆም ጊዜ በሚያይህ፡፡
- 219. በሰጋጆች ውስጥ መዘዋወርህንም (በሚያየው ጌታህ ላይ ተጠጋ)፡፡
- 220. እነሆ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡
- 221. ሰይጣናት በማን ላይ እንደሚወርዱ ልንገራችሁን
- 222. በውሸታም ኀጢአተኛ ሁሉ ላይ ይወርዳሉ፡፡
- 223. የሰሙትን (ወደ ጠንቋዮች) ይጥላሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም ውሸታሞች ናቸው፡፡
- 224. ባለ ቅኔዎችንም ጠማማዎቹ ይከተሉዋቸዋል፡፡
- 225. እነርሱ በ(ንግግር) ሸለቆ ሁሉ የሚዋልሉ መኾናቸውን አታይምን
- 226. እነሱም የማይሠሩትን ነገር የሚናገሩ መኾናቸውን (አታይምን)፤
- 227. እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ አላህንም በብዛት ያወሱ ከተበደሉም በኋላ (በቅኔ) የተከላከሉ ሲቀሩ፤ (እነርሱ አይወቀሱም)፡፡ እነዚያም የበደሉ (ከሞቱ በኋላ) እንዴት ያለን መመለስ እንደሚመለሱ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡